Fana: At a Speed of Life!

የዜጎችን ሁለንተናዊ መብትና ጥቅም ለማስከበር የመንግስት ተቋማት በትኩረት ሊሰሩ ይገባል- ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የዜጎችን ሁለንተናዊ መብትና ጥቅም ለማስከበር የመንግስት ተቋማት በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ አሳሰቡ።

ለመንግስት ተቋማት መካከለኛ የስራ ኃላፊዎች በፌደራል አስተዳደር ሥነ- ሥርዓት  አዋጅ አስፈላጊነት እና አተገባበር አስመልክቶ የስልጠና መድረክ መካሄዱን ከጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በስልጠናው ላይ የተገኙት ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዶክተር ጌዲዮን፥ የፌደራል አስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጁ በመንግስት ተቋማት ላይ ግዴታ የሚጥል፣ ለዜጎች ደግሞ መብት የሚሰጥ በመሆኑ ተግባራዊነቱ ላይ ችላ ማለት አይገባም ብለዋል፡፡

የስልጠና መድረኩ አዋጁን ለመረዳት እና ተግባራዊ ለማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው፤ የአዋጁን አላማ ለማሳካት በየተቋማቱ የሚገኙ ከፍተኛ እና መካከለኛ ስራ  ኃላፊዎች በመተሳሰር ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባቸውም ተናግረዋል፡፡

ዶክተር ጌዲዮን አክለውም ሁሉም የአስተዳደር ተቋማት ስራ ላይ ያሉ እና አዲስ የሚወጡ መመሪያዎችን በፍጥነት ለኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መስሪያ ቤት መላክ እንደሚገባቸው አስታውቀዋል።

እንዲሁም ተቋማት መመሪያ ሲያወጡና አስተዳደር ውሳኔ ሲወስኑ በሥነ-ሥርዓት አዋጁ መሰረት ሊሆን ይገባልም ነው ያሉት።

የአስተዳደር ተቋማት በሚሰጡት አስተዳደራዊ ውሳኔዎችና መመሪያዎች ቅር የተሰኘ ማንኛውም ዜጋ የውሳኔዎቹንና የመመሪያዎችን ሕጋዊነት በፍርድ ቤት ማስመርመር እንደሚችል የተደነገገ በመሆኑ ከሚፈጠር የፍርድ ቤት ጫና በትኩረት በመስራት የዜጎችን መብት ማስከበር እንደሚገባም አሳስበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.