Fana: At a Speed of Life!

የደም ማነስ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 6፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)የደም ማነስ ምልክቶች እንደደም ማነስ አይነቶች ይለያያል፡፡

መነሻው፣ የበሽታው ከባድነት እና ማንኛውም የጤና ችግር(ክንታሮት፣ ቁስለት፣ የወር አበባ ችግር ወይም ካንሰር የመሳሰሉት) አስተዋጽዎ ያደርጋሉ።

የደም ማነስ በሽታው ቀለል ያለ ከሆነ ወይም ከብዙ ጊዜ በፊት ከተከሰተ ምንም አይነት ምልክት ላይታይ ይችላል።

ለማንኛውም አይነት የደም ማነስ የጋራ የሆኑ ምልክቶችም የድካም ስሜት እና ጉልበት ማጣት፣ ያልተለመደ ፈጣን የልብ ምት በተለይ እንቅስቃሴ ሲደረግ፣ የትንፋሽ ማጠር እና ራስ ምታት፣ የትኩረት ማጣት፣ የማዞር ስሜት፣ የቆዳ መገርጣት፣ የእግር ጡንቻ መሸማቀቅ አና የእንቅልፍ ማጣት ይጠቀሳሉ፡፡

በብረት እጥረት የሚከሰት የደም ማነስ ያለባቸው ሰዎች ምልክቶች ባልተለመደ ሁኔታ ወረቀት፣ በረድና ቆሻሻዎችን ለመመገብ መፈለግ፣ ጥፍሮቻችን ወደላይ መታጠፍ(መበላሸት)፣ የአፍ መሰነጣጠቅ እና መቁሰል ናቸው፡፡

በቫይታሚን ቢ 12 እጥረት የሚከሰት የደም ማነስ ያለባቸው ሰዎች በእጅና እግር ላይ መርፌ የመወጋት ስሜት መሰማት፣ የመዳሰስ ስሜት ማጣት፣ መንቀጥቀጥ እና ለመራመድ መቸገር እና የእጅና እግር መጠንከር(መገተር) እንደምልከቶች ይጠቀሳሉ፡፡

በሊድ(lead) መመረዝ የሚከሰት የደም ማነስ ሰማያዊ_ጥቁር መስመር በድድ ላይ መኖር፣ የሆድ ህመም፣ የሆድ ድርቀት እና ማስታወክ የበሽታው ምልክቶች ናቸው፡፡

በቀይ የደም ሴሎች ውድመት የሚከሰት የደም ማነስ የአይን እና ቆዳ ቢጫ መሆን፣ ቡናማ ወይም ቀይ ሽንት፣ የእግር ቁስለት፣ ህፃናት እንዳይፋፉ/እንዳይዳብሩ መሆን እና የኩላሊት ጠጠር በሽታ አይነት ምልክቶች ይታያሉ፡፡

የሲክል ሴል የደም ማነስ ምልክቶች፣ የድካም ስሜት፣ ለኢንፌክሽን መጋለጥ፣ በህፃናት ላይ የዕድገት እና ብስለት መዘግየት፣ የመገጣጠሚያ፣ ሆድ፣ እጅና እግር በተወሰነ ቆይታ በተደጋጋሚ ከባድ የህመም ስሜት መከሰት ናቸው፡፡

በርግጥ የደም ማነስ ህክምና እንደመነሻው ይወሰናል፡፡

በብረት እጥረት የሚከሰት የደም ማነስ የአመጋገብ ስርዓታችንን እና ብረት በመውሰድ ማከም ይቻላል።

ይህ የብረት እጥረት የተከሰተው ከወር አበባ ውጪ በሆነ የደም መፍሰስ ከሆነም የሚፈስበትን ቦታ ማወቅ እና እንዲቆም ማድረግ ተገቢ መሆኑን ከደቡብ ክልል ጤና ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.