Fana: At a Speed of Life!

የደረሱ ሰብሎች ጉዳት ሳይደርስባቸው እንዲሰበሰቡ ሁሉም ሊረባረብ ይገባል- አቶ ኡመር ሁሴን

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የደረሱ ሰብሎች ጉዳት ሳይደርስባቸው እንዲሰበሰቡ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሊረባረብ እንደሚገባ የግብርና ሚኒስትር አቶ ኡመር ሁሴን ተናገሩ።

ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዜና መጽሄት ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ የዘንድሮ የመኸር ምርት በተለይም በትርፍ አምራች አካባቢዎች በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ አስታውቅዋል።

በሀገሪቱ በተለያዩ አከባቢዎች የደረሰው ስብል በአንበጣ መንጋ ጉዳት ሳይደርስበት መሰብሰብ እንደተጀመረ የገለፁት አቶ ኡመር፥ የምርት መሰብሰብ ስራውም በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን አስታውቅዋል።

በምርት ስብሰባውም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ ወጣቶች፣ የመከላከያ ሰራዊትን ጨምሮ ሌሎችም የፀጥታ አካላይ አንዲሁም በጎ ፍቃደኞች እየተሳተፉ መሆኑንም ገልፀዋል።

በቀጣይም የደረሱ ሰብሎችን ለመሰብሰብ በሜካናይዜሽን እና ሌሎችም ዘዴዎችን በመጠቀም ለመሰብሰብ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አቶ ኡመር ተናግረዋል።

ከአንበጣ መንጋ ጋር በተያያዘም፤ መንጋውን ለመቆጣጠር እስካሁን በርካታ ስራዎች መሰራቱንም ሚኒስትሩ አስታውቅዋል።

እስካሁን በተሰራው ስራም የአንበጣ መንጋ በተከሰተባቸው በምስራቅ አማራ፣ በአፋር ክልል እንዲሁም ምስራቅ ኦሮሚያ እስከ 80 በመቶ የመቆጣጠር ስራ መሰራቱን አብራርተዋል።

ይሁን እንጂ በምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል የሚገኘው የአንበጣ መንጋ ወደ ሶሜሌ ድንበር በመሄድ እንቁላል በመጣል ራሱን ዳግም ሊያራባ እንደሆነም ገልፀዋል።

ይህንን ጨምሮ መንጋው በሌሎች አካባቢዎችም ዳግም እንዳይከሰት ተከታትሎ የማጥፋት ስራ እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን አክለውም፥ በአንበጣ መንጋው ሰብላቸው የወደመባቸው አርሶ አደሮች ልየታ እየተካሄደ መሆኑንም ገልፀዋል።

ጉዳት ለደረሰባቸው አርሶ አደሮችም በሁለት መልኩ ድጋፍ እንደሚደረግ በመግለጽ፤ ከዚህም አንደኛው አርሶ አደሮች በበጋ እንዲያመርቱ መደገፍ ነው ብለዋል።

አርሶ አደሮች በበጋ እንደሚያመርቱም ዘር ጨምሮ የውሃ መሳቢያ ፓምፖች እና ሌሎችም የሜካናይዜሽን መሳሪያዎች ድጋፍ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

በተጨማሪም ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመሆን ጉዳት ለደረሰባቸው አርሶ አደሮች የእለት ደራሽ ድጋፍ ለማድረስ እየተሰራ መሆኑንም አስታውቅዋል።

አርሶ አደሩ በቀጣይ የአንበጣ መንጋን ከመከላከል ጎን ለጎን የግብርና ስራው ላይ ትኩረት ሊያደርግ እንደሚገባም አቶ ኡመር አሳስበዋል።

በሙለታ መንገሻ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.