Fana: At a Speed of Life!

የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተወያዩ።

በውይይቱ አቶ እርስቱ ይርዳ እንደተናገሩት የመንግስትና የተፎካካሪ ፓርቲዎች የጋራ ውይይት በክልሉ የሚስተዋሉ የሰላም መደፍረሶችን ከማስቀረት ባለፈ በጋራ ጉዳዮች በመምከር ችግርን አስቀድሞ የመፍታት ልምድ ያዳብራል ፡፡

ተፎካከሪ ፓርቲዎችን ወክለው የመጡትን ህብረተሰብ የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝና በጋራ የተጀመረው ለውጥ ከዳር እንዲደርስ ሚናቸው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

እንዲሁም ሀገር መቀጠል የምትችለውና ልማት ሆነ ዲሞክራሲያዊና ፍትሀዊ ምርጫ ማካሄድ የሚቻለው በሁሉም አካባቢ ሰላምን በማስፈን በመሆኑ ተፎካካሪ ፓርቲዎች አባላቶቻቸውንም ሆነ ደጋፊዎቻቸው ሰላምን በማድፍረስ ስራ እንዳይሳተፉና የሴራ ፖለቲካን ከሚያራምዱ በመጠበቅ የክልሉ ሰላም እንዲጠበቅ መስራት ይጠበቅባቸዋል ሲሉ ተናግረዋል ፡፡

ከዚህም ጎን ለጎን መንግስትን የህዝብን ደህንነት ለመጠበቅ ምርጫ በመራዘሙ ምክንያት መስከረም 30 በኋላ መንግስት የለም የሚሉና በጉልበት መንግስት ለመናድ የሚሰሩ ቡድኖችን ሊታገሉ ይገባል ብለዋል፡፡

የደቡብ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ በበኩላቸው በክልሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የተቋቋሙት የክልሉን ህዝብ ፍላጎት ከዳር ለማድረስ በመሆኑ የጋራ መድረኮችን በማዘጋጀት በሚያጋጥሙ ችግሮችና መፍትሔቻቸው ላይ በጋራ እየመከሩ መስራቱ አስፈላጊ ነው፡፡

አቶ ማቲዎስ ባልቻ የወላይታ ብሔር ንቅናቄ የስራ አስፈፃሚ እንዳሉት ሰላም የጋራ እሴት በመሆኑና ሰላም ከሌለ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ማድረግ አዳጋች በመሆኑ ለሰላም መድፍረስ መንስኤ የሆኑ ጉዳዮችን በመለየት ከመንግስት ጋር መምከራቸው ጠቃሚ መሆኑን ጠቁመው መንግስት በፍትህ አካላት አካባቢ የሚታየውን የህግ መላላት ሊከታተል ይገባል ብለዋል፡፡

አቶ ብርሀኑ ዘለቀ የሞቻ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ፕሬዝዳንት በበኩላቸው በክልሉ የሚገኙ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የየአካባቢያቸውን ማህበረሰብ ከመወከል ባለፈ እንደ ሀገር የላቀ አበርክቶ ለማድረግ ይበልጥ ለመሰማት በተናጥል ከመሄድ ይልቅ በጋራ መስራት እንደሚጠበቅባቸውም ገልዋል፡፡

እንዲሁም ከመንግስት አመራሮች የሚደርሰውን እስርና እንግልት ለማስቀረት መሰራት እንዳለበት ገልፀው ሀሳባቸውንና ዓላማቸውን ለመግለጽ የሚያስችል የአቅም ውስንነት በመኖሩ መንግስት ከፅ/ቤት ማደራጀት ጀምሮ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡

የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት ወንጀል ሰርተው ፓርቲያቸውን መሸሸጊያ ማድረግ እንደሌለባቸው የገልፁት ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ርስቱ ይርዳ ያለጥፋት የታሰሩም ካሉ የክልሉ መንግስት ኃላነቱን እንደሚወጣ አሳስበዋል።

በውይይቱ ብልፅግና ፓርቲን ጨምሮ 9 ተፎካከሪ ፓርቲዎች የተገኙ ሲሆን በቀጣይም እንደሀገር የተደራጁና በክልልሉ የሚገኙ ፓርቲዎችን ጭምር እንዲሳተፉ አቶ ርስቱ ይርዳ ጥሪ ማቅረባቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዬች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.