Fana: At a Speed of Life!

የደቡብ ክልል ብሄርን እና ሀይማኖትን ሽፋን በማድረግ ሁከት ለመፍጠር በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ ጠንካራ እርምጃ እንደሚወስድ አስታወቀ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 24 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግስት ብሄርን እና ሀይማኖትን ሽፋን በማድረግ ሁከት ለመፍጠር በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ ጠንካራ እርምጃ እንደሚወስድ አስታወቀ።
የክልሉ መንግስት ባወጣው መግለጫ ሀገራችን ኢትዮጵያ ብዙ ቋንቋዎች የሚነገሩባት፣ ብዝሃ ባህሎች፣ ታሪኮችና ኃይማኖቶች ያሉባት ሀገር መሆኗን አስታውቋል።
ብዝሃነታችን በህብረተሰቡ መካከል መቻቻልን፣ መከባበርንና መደጋገፍን አልፎም የህብረ ብሔራዊ አንድነታችን መገለጫ እንጅ ለመገፋፋትና ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ለማድረስ ምክንያት አይሆንም ብሏል በመግለጫው።
የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦
መንግስት ብሄርን እና ሀይማኖትን ሽፋን በማድረግ ሁከት ለመፍጠር በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ ጠንካራ እርምጃ ይወስዳል
ሀገራችን ኢትዮጵያ ብዙ ቋንቋዎች የሚነገሩባት፣ ብዘሃ ባህሎች፣ ታሪኮችና ኃይማኖቶች ያሉባት ሀገር ነች።
ብዝሃነታችን በህብረተሰቡ መካከል መቻቻልን፣ መከባበርንና መደጋገፍን አልፎም የህብረ ብሔራዊ አንድነታችን መገለጫ እንጂ ለመገፋፋትና ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ለማድረስ ምክንያት አይሆንም ።
ሀገራችን ኢትዮጵያ ጥንትም ሆነ ዛሬ በየጊዜው የሚገጥሟትን ፈተናዎች እየተሻገረች ሉዓላዊነቷን አስከብራ ኖራለች።
በነጻነቱ የማይደራደረው የሀገራችን ህዝብ በዘር፣በጎሳ እና በሀይማኖት ሳይከፋፈል ጠላትን እየመከተ ታፍራና ተከብራ የኖረች ሉዓላዊት ሀገር አስረክቦናል።
በህዝቦቿ ደም እና አጥንት የተገነባችን ሀገር ለማፍረስ ጠላት ሌት ተቀን እየተጋ ነው። በግልጽ ጦርነት ከማወጅ ጀምሮ በሁሉም ዘርፍ ረጃጅም እጆቹን እያስገባ ህዝብ እንዲሸበር እና ሀገር እንዳትረጋጋ በማድረግ ላይ ይገኛል።
የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጠላቶች የሀገራችንን የእድገት ጉዞ ለማደናቀፍ ሴራ ሸርበው እና ወጥመድ ዘርግተው ያለ የሌለ ሀይላቸውን እየተጠቀሙ ነው።
ሀገር እንዳይረጋጋ በህዝቦች መካከል ጥርጣሬ እንዲፈጠር እና ሀገሪቱን የትርምስ ቀጠና ለማድረግ ሁሉንም አማራጮች በመጠቀም ህዝብ እንዲሸበር በመስራት ላይ ናቸው።
ለሴራቸው ማሳኪያ ከሚጠቀሙባቸው መንገዶች አንዱ በሃይማኖት ሽፋን ከውጪ ኃይሎች ጋር በማበር የጥፋት በትራቸውን እያሳረፉ ነው ።
በቅርቡ በክልላችን ስልጤ ዞን የተከሰተው ችግር አንዱ ማሳያ ነው።
ለዘመናት ተቻችለው፣ ተከባብረውና ተደጋግፈው በሚኖሩ ሙስሊምና ክርስትያን ህዝቦች መካከል ፀብ በማጫር በኃይማኖት ሽፋን እኩይ ዓላማቸውን ለማስፈጸም የገቡ ኃይሎች ሴራ በህብረተሰቡ ተሳትፎ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ ማክሸፍ ተችሏል።
መንግስት ብሄርን እና ሀይማኖትን ሽፋን በማድረግ ሁከት ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱት አካላትን በመለየት ለህግ የሚያቀርብ ሲሆን በአጥፊዎች ላይ ጠንካራ እርምጃ ይወስዳል።
መላው የክልላችን ህዝብ በሀይማኖት ተቋማት እና በምዕመናን ላይ እየተሰነዘረ ያለውን ጥቃት በማውገዝ ከዚህ ቀደም የነበረንን የመቻቻል፣ የመከባበር እና የአንድነት እሴቶች ማጎልበት ይኖርበታል።
አንድ ስንሆን ጠላቶቻችን ያፍራሉ፣ አንድ ስንሆን ጥንካሬያችን ይጎላል፣ አንድ ስንሆን የጠላት ሀይል ይዳከማል፣ አንድ ስንሆን ወደምንፈልገው እድገት እንሸጋገራለን።
መላው የክልላችን ህዝቦች ከመንግስት ጎን በመሆን ኢትዮጵያን ለማተራመስ ፍላጎት ያላቸውን ሀይሎች እንዲታገሉ የክልሉ መንግስት ጥሪ ያቀርባል።
ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለ1443ኛው የኢድ አል ፈጥር በዓል በሰላም አደረሳችሁ!!
በድጋሚ ኢድ ሙባረክ!!
ሚያዝያ 24/2014
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.