Fana: At a Speed of Life!

የደቡብ ክልል ተለያዩ ዞኖች ከአጎራባች ሕዝቦች ጋር ክልል ሆኖ ለመደራጀት በየምክር ቤቶቻቸው ውሳኔ አሳለፉ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የተለያዩ ዞኖች ከአጎራባች ሕዝቦች ጋር ክልል ሆኖ ለመደራጀት በየምክር ቤቶቻቸው ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡

የጎፋ ዞን ህዝብ ምክር ቤት 4ኛ ዙር 9ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 5ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው።

በዚህም ምክር ቤቱ የክልል አደረጃጀትን በተመለከተ በደቡብ ክልል ከሚገኙ ከሌሎች አጎራባች ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ጋር አብሮ ለመደራጀት የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ በሙሉ ድምጽ አፅድቋል።

የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር ጌትነት በጋሻው በአዲስ የክልል አደረጃጀት በጋራ ለሚደራጁ 11 መዋቅሮች ወላይታ፣ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ጌዴኦ፣ ኮንሶ፣ አማሮ፣ ደቡብ ኦሞ፣ አሌ፣ ባስኬቶ፣ ቡርጂ እና ደራሼ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የማዕከል ጉዳይ ሳይንሳዊ፣ ምክንያታዊ በሆነ እንዲሁም ውይይት ተደርጎበት በህዝብ ድምፅ የሚወሰን መሆኑን ዶክተር ጌትነት የገለፁ ሲሆን÷ የክልል አደረጃጀት ጥያቄ የሕዝቡን ጥቅም ባስከበረ መልኩ እንዲሆን መንግስት ትኩረት ሰጥቶ መመልከቱን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ የስልጤ ዞን ምክር ቤት እያካሄደ በሚገኘው 4ኛ ዙር 22ኛ መደበኛ ጉባዔ የክልል አደረጃጀት ጥያቄን ለመመለስ በመፍትሄነት በቀረበዉ መነሻ የውሳኔ ሀሳብ ላይ ከተወያየ በኋላ የውሳኔ ሀሳቡን ተቀብሎ አጽድቆታል ።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ ከድር የስልጤ፣ የጉራጌ፣ የሀዲያ፣ የካምባታ ጠምባሮ ፣ የሀለባ ዞኖች እና የም ልዩ ወረዳ ሕዝቦች ካለቸዉ መልካም ምድራዊና ሥነ ልቦናዊ የጋራ መስተጋብር አንፃር በአንድ አደረጃጀት እንዲሆኑ የሚል የዉሳኔ ሀሳብ መቅረቡን አብራርተዋል።

የዞን ምክር ቤቱ የክልል አደረጃጀት ጥያቄን ለመመለስ በመፍትሄነት የቀረበዉን መነሻ ሀሳብ ይኸውም ስልጤ፣ ጉራጌ፣ ሀዲያ፣ ካምባታ ጠምባሮ ፣ ሀለባ ዞኖች እና የም ልዩ ወረዳ አንድ ላይ ይደራጁ የሚለዉን መነሻ የዉሳኔ ሀሳብ በአንድ ተቃዉሞ በአብላጫ ድምጽ ተቀብሎ ማፅደቁን ከደቡብ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የደቡብ ክልል መንግስት ሰሞኑን የክልል አደረጃጀትን አስመልክቶ በዞን እና በልዩ ወረዳ ምክር ቤቶች የተላለፉ ውሳኔዎችን “በሳል ውሳኔ” ሲል አድናቆት እና ምስጋና ማቅረቡ ይታወቃል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.