Fana: At a Speed of Life!

የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በአጣዬና አካባቢው ከመኖሪያ ቀያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በአጣዬና አካባቢው ከመኖሪያ ቀያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች ከ8 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርጓል፡፡

የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በአጣዬና አካባቢው ቡድን አዋቅሮና ችግሮችን በጥናት እየለየ ተከታታይ የድጋፍ ሥራዎችን በማከናውን ላይ እንደሚገኝ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባዩ ጌታሁን ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ከአሁን በፊትም ለተጎጂዎቹ ምግብና ቁሳቁስ በማቅረብ ድጋፍ ማድረጉን ነው ሃላፊው የገለጹት፡፡

በአራተኛ ዙር ድጋፉ የዩኒቨርሲቲውን ሠራተኞች፣ መምህራንና ተማሪዎችን በማስተባበር ልዩ ልዩ አልባሳትና ከግማሽ ሚሊየን ብር በላይ ገንዘብ በማሰባሰብ በተወካዮች በኩል ድጋፍ መደረጉን አንስተዋል፡፡

የአጣዬ ከተማን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ሁሉን አቀፍ ጥረት የክልሉንና የዞኑን መንግሥት ለማገዝ በዩኒቨርሲቲው ተከታታይ የድጋፍ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉም ነው ያሉት፡፡

የአሁኑ ድጋፍ ከ4 ሚሊየን ብር በላይ እንደሚገመት የገለጹት ሃላፊው÷ በአጠቃላይ ለአራት ጊዜ በተደረጉ ድጋፎች በቁሳቁስና በጥሬ ገንዘብ ከ8 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ መደረጉን አንስተዋል፡፡

የአጣዬ ከተማ ከንቲባ አቶ አገኘሁ መክቴ በበኩላቸው ÷ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በአጣዬና አካባቢው የደረሰውን ጉዳት ግምት ውስጥ በማስገባት በጥናት ላይ የተመሰረቱ ድጋፎችን በማድረግ ከሕዝቡ ጎን መቆሙንም አንስተዋል፡፡

ዛሬ የተደረጉት ድጋፎችም አጣዬ ከተማን መልሶ ለማደራጀትና ጉዳት የደረሰባቸውን አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሥራ ለማስጀመር እንደሚውሉ መናገራቸውን ከዩኒቨርሲቲው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.