Fana: At a Speed of Life!

የዲጂታል ዲፕሎማሲውን ከመደበኛው ዲፕሎማሲ ጋር በጣምራ ለማስኬድ ትኩረት ተሰጥቷል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ)የዲጂታል ዲፕሎማሲውን ከመደበኛው ዲፕሎማሲ አሰራር ጋር በማጣመር ውጤታማ የዲፕሎማሲዊ ሥራ ለማከናወን ትኩረት መሰጠቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለኢዜአ እንደተናገሩት፥ ሚኒስቴሩ በቀጣይ የዲጂታል ዲፕሎማሲን በአግባቡ ለመጠቀም ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል።
በተለይም ከመደበኛው የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ጋር በማጣመር ከዘመኑ ጋር አብሮ ሊሄድ የሚችል ቀልጣፋና ውጤት ተኮር የዲፕሎማሲ ሥራ ለመሥራት መታቀዱን አስረድተዋል።
በዚህም ዲፕሎማቶች ዲጂታል ዲፕሎማሲውን ከመደበኛ ሥራቸው ጋር አጣምረው እንዲቀጥሉ የሚያስችላቸው ሥልጠና እየተሰጣቸው መሆኑን ጠቁመዋል።
አገር ቤት ለተጠሩት ለዲፕሎማቶቹ የሚሰጡት የዲጂታል ዲፕሎማሲውና ሌሎች የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች አቅማቸውን ለማዳበር የሚያስችላቸው መሆኑንም ተናግረዋል።
ይህም የአገሪቷን ገጽታ ሁሉን አቀፍ በሆነ መልኩ ለማስተዋወቅና ብሔራዊ ጥቅም በአግባቡ ለማስከበር የሚያስችል መሆኑን ነው አምባሳደር ዲና የገለጹት።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ይግዛው በበኩላቸው፥ ዲፕሎማቶቹ ዘመናዊውን የዲጂታል ዲፕሎማሲ መቀላቀል አለባቸው ብለዋል።
ዲጂታል ዲፕሎማሲ ወጪ ቆጣቢ፣ ለአጠቃቀም አመቺና በቀላሉ መልዕክትን ለተደራሽ የሚያደርግ በመሆኑ ዲጂታል ዲፕሎማሲን ማጎልበት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በዚህም የሚኒስቴሩን ተልዕኮ በብቃት ለመወጣት አጠቃቀሙን በተገቢው መልኩ ማወቅና የሚተላለፉትን መልዕክቶችም በአግባቡ መቃኘት እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።
በሌላ በኩል ዲጂታል ዲፕሎማሲ የታለመለትን ግብ እንዲመታ የደኅንነት ጉዳዮችን በአግባቡ በማጤን ለሳይበር ጥቃት ተጋላጭነትን መቀነስ እንደሚገባ ነው የተናገሩት።
በተለይም ማኅበራዊ ሚዲያውን በአግባቡና በምስጢራዊነት መጠቀም እንዲሁም የተቋሙን የማኅበራዊ ሚዲያ የሚያስተዳድሩ አካላትን ሥነ-ምግባር መከታተል እንደሚገባ አሳስበዋል።
የሳይበር ጥቃቶችን ለመከላከል ተቋማቸው አስፈላጊውን ክትትል እንደሚያደርግ ገልጸው ሁነኛ መፍትሄው ግን የቴክኖሎጂና የእውቀት ባለቤት መሆን ነው ብለዋል።
ለዚህም መንግሥት ከሚያደርገው ጥረት በተጨማሪ የሚመለከታቸው አካላት እንዲሳተፉ ዶክተር ሹመቴ ጠይቀዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሁን ላይ የሚታዩ የዲጂታል ዲፕሎማሲው ትሩፋቶችን ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
0
People Reached
0
Engagements
Boost Post
Like

Comment
Share
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.