Fana: At a Speed of Life!

የዲጅታል ዲፕሎማሲውን ለማጠናከር ያለመ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ማዕከል ተቋቋመ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 11 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የምሁራን ሚና ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የበይነ መረብ ምክከር እየተካሄደ ነው፡፡

ውይይቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጋር በመተባበር አዘጋጅተውታል፡፡

በውይይቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ ፣የውኃ፣ መስኖ እና ኢነርጅ ሚኒስትር ዶ/ር ኢ/ር ስለሽ በቀለን ጨምሮ ከሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ የሥራ ኀላፊዎች እየተሳተፉ ነው።

በዚህም የህዳሴ ግድብን ተከትሎ እየደረሰ የሚገኘውን ጫና ለመመከት የሚያስችል እና የዲጅታል ዲፕሎማሲውን ለማጠናከር ያለመ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ማዕከል ተቋቁሟል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን÷ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ማእከል ሁሉም ዜጋ ዲፕሎማት ነው የሚለውን ሐሳብ እንደሚያጠናክር ተናግረዋል፡፡

ሁሉም ኢትዮጵያውያን ህልማቸውን እውን ለማድረግ እውቀታቸውን፣ ጉልበታቸውን እና ሃብታቸውን አስተባበረው ግድቡን እውን ሊያደረጉ እየተጉ መሆኑንም አውስተዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን የዚህን ፍሬ ለማየት ወደተራራው እየዘለቁ ባሉበት ወቅት የኢትዮጵያን እድገት የማይፈልጉ አካላት ከዚህ ለመመለስ የሐሰት መረጃዎችን በማሰራጨት ላይ ይገኛሉም ነው ያሉት።

ግብጽ ኢትዮጵያውያን ፍሬያቸውን እንዳያዩ ያለ የሌለ አቅሟን እየተጠቀመች ትገኛለች ያሉት አቶ ደመቀ÷ ይህ ማእከልም የግብጽ እና መሰሎቿን ሴራ ለመቋቋም ምሁራኖችን ከተማሪዎች ጋር ለማቀናጀት ጠቀሜታው ላቅ ያለ ነው ብለዋል።

ማዕከሉ የበሰሉ ኢትዮጵያዊ ዲፕሊማቶችን ለማፍራትም ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው መጠቆማቸውን ከደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ በበኩላቸው÷ ምሁራን ለሀገራቸው የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ እያደገ መምጣቱን አንስተዋል፡፡

ምሁራኑ ይህንን ሚና በማሳደግ ኢትዮጵያ እና አፍሪካን የማንቃት ሚናቸውን በተገቢው መንገድ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የውኃ፣ መስኖ እና ኢነርጅ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ስለሽ በቀለም አሁን ላይ ዝናብ በአስተማማኝ እና ከመደበኛ በላይ እያገኘን በመሆኑ የግድቡ ሁለተኛ የውኃ ሙሌት ያለምንም ችግር እንደሚከናወን አረጋግጠዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.