Fana: At a Speed of Life!

የጃፓን መንግስት ለዓለም አቀፍ ሠላም ማስከበር ማሠልጠኛ ተቋም ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የጃፓን መንግሥት ለዓለም አቀፍ የሠላም ማስከበር ማሠልጠኛ ተቋም የ850 ሺህ ዶላር ድጋፍ አደረገ።
የገንዘብ ድጋፉ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት መርኃ ግብር በኩል የሚያልፍ ሲሆን፤ ለማሠልጠኛ ተቋሙ አቅም ግንባታ እንደሚውል ተገልጿል።
በመከላከያ ሚኒስቴር የዓለም አቀፉ የሠላም ማስከበር ማሰልጠኛ ተቋም ኃላፊ ብርጋዴር ጄኔራል ሰብስቤ ዱባና የመንግሥታቱ ድርጅት የልማት መርኃ ግብር ምክትል የኢትዮጵያ ተወካይ ሴሌኦፋስ ቶሮሪ የድጋፍ ሥምምነቱን ተፈራርመዋል።
ብርጋዴር ጄኔራል ሰብስቤ ድጋፉ በቀዳሚነት ለተቋሙና በውስጡ ለሚገኘው የሰው ኃይል አቅም ግንባታ እንደሚውል ተናግረዋል።
ተቋሙ የሠላም ማስከበር ተልዕኮውን ውጤታማ ማድረግ የሚያስችሉ ሥልጠናዎች ለመስጠትና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ድጋፉ አቅም እንደሚሆን ፤በተጨማሪም በዓለም አቀፍ የሠላም ማስከበር ተልዕኮ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመሙላትና ቀጣናዊ የተጠባባቂ ኃይልን ለመደገፍ እንደሚያግዝም ገልጸዋል።
የጃፓን መንግሥት ተመሳሳይ የሥልጠና መርሃ ግብር ድጋፎችን እያደረገ መሆኑን አስታውሰው፤ ይህ “አጋርነት ሊቀጥል ይገባል” ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የተመድ የልማት መርኃ ግብር ምክትል የኢትዮጵያ ተወካይ ሴሌኦፋስ ቶሮሪ በበኩላቸው የተደረገው ድጋፍ ጃፓን ለዓለም በተለይም ለአፍሪካ ሠላምና ደኅንነት ጉዳዮች ያላትን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ አገራቸው የአፍሪካን በተለይም የምስራቅ አፍሪካን ሠላምና ደኅንነት ለማስከበር በትኩረት እንደምትሰራ ገልጸዋል።
ይህንን ለማድረግና የሠላም ተልዕኮውን ለማጠናከር ጃፓን ከመከላከያ ዓለም አቀፍ የሠላም ማስከበር ማሠልጠኛ ተቋም ጋር በጋራ እየሰራች መሆኗን ጠቅሰው ጃፓን ከማሠልጠኛ ተቋሙ ጋር ያላትን አጋርነት አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.