Fana: At a Speed of Life!

የገበያ ንረት የሚፈጥሩ አካላትን መንግስት እንዲቆጣጠር የደቡብ ክልል ነዋሪዎች ጠየቁ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 16፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የገበያ ንረት እንዲፈጠር የሚያደርጉ አካላትን መንግስት ሊቆጣጠር እንደሚገባ የደቡብ ክልል ነዋሪዎች አሳሰቡ።

በገበያ ውስጥ ተሳትፎ ያላቸውን ማህበራት ማጠናከር ገበያውን ለማረጋጋት አማራጭ መሆኑን ነዋሪዎች ጠቁመዋል።

ህዝቡም ከመንግስት ጎን መሆን እንዳለበት ያሳሰቡት ነዋሪዎቹ፥ ነጋዴው ማህበረሰብም ገበያውን በማረጋጋቱ ረገድ የበኩሉን ድርሻ መወጣት አለበት ብለዋል።

ከቁጥጥር ተግባራት ባለፈ የአቅርቦትና የፍላጎት መጣጣምን በመፍጠር ችግሩን ለመቅረፍ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታውቋል።

የቢሮው ምክትል ሀላፊ አቶ ይግለጡ አምዛ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትጋር በነበራቸው ቆይታ፥ ለዋጋ ጭማሪው ሌሎች ምክንያቶች ቢኖሩም ሰው ሰራሽ አስተዋፅኦ እንዳላቸው ገልፀዋል።

ሸማቹ ህብረተሰብ ዋጋ ሲጨመርበት ለምን ሊጨምር እንደቻለ የመጠየቅ ልምድ ማዳበር እንዳለበትም አሳስበዋል።

ሆን ብለው ምርት በማከማቸት የዋጋ ንረት በሚፈጥሩ አካላት ላይም እንደ አግባብነቱ እርምጃ እንደሚወሰድ በመግለፅ የምርት እጥረት ሳይኖር የዋጋ ጭማሪ መታየቱ ተገቢነት የለውም ተብሏል።

የተለያዩ ምርቶችን ለህብረተሰቡ የሚያቀርቡ ማህበራትን በማጠናከርም ለውጥ መፍጠር እንደሚቻል ምክትል የቢሮ ሃላፊው የመጋዘን እጥረትና መሰል ክፍተቶቻቸውን መቅረፍ እንዲችሉ እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል።

በብርሃኑ በጋሻው

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.