Fana: At a Speed of Life!

የገቢዎች ሚኒስቴር በአስር ዓመት የብልፅግና መሪ ዕቅድ ላይ ተወያየ

አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የገቢዎች ሚኒስቴር ከተጠሪ ተቋመቱ ጋር በአስር ዓመት የብልፅግና መሪ ዕቅድ ላይ መወያየቱን አስታወቀ፡፡

የኢፌዴሪ የገቢዎች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዘመዴ ተረፈ÷ ሚኒስቴር ሚስሪያ ቤቱና ተጠሪ ተቋመቱ (ጉምሩክ ኮሚሽንና ብሔራዊ ሎተሪ) ሀገራዊ የብልፅግና ዕቅዱን እና የባለፉት ዓመታት የገቢ ዘርፉን አፈጻጸም መነሻ በማድረግ የ10 ዓመት መሪ ዕቅድ ማዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

ተቋሙ የተገልጋዮችን እርካታ በማሳደግና የመንግስትን ገቢ በብቃት ለመሰብሰብ የሚያስችሉ በርካታ የአገልግሎት አሰጣጥ ሪፎርም ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ሃላፊው አያይዘውም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የብልጽግና ዕቅዱን እንደ መነሻ የወሰደው ኢትዮጵያ ፤ የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት የሚለውን የአገራዊ የብልጽግና ራዕይ መሆኑን ጠቁመው ÷ይህንን እንደ መነሻ በማድረግ የገቢዉ ዘርፍ ወደ ሀገራዊ ራዕይ የሚያደርሱ የትኩረት አቅጣጫዎችና ግቦችን ቀርጾ ለተግባራዊነቱ ከምን ጊዜዉም በላይ እየሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

የሀገሪቱ የታክስ አስተዳደር ስርዓት በኢ- መደበኛ ኢኮኖሚ፣ በህገ-ወጥ ንግድ፣ በታክስ ማጭበርበር እና በኮንትሮባንድ ምክንያት የተፈጠሩ ችግሮችን በማስተካከል የመወዳደሪያ ሜዳውን እኩል ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ስራዎች እንደሚሰራም ተገልጿል።

እቅዱን ለማሳካት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና ተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ሠራተኞች እንዲሁም የግብር ከፋዮቹና የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ሃላፊው ገልጸዋል።

በተጨማሪም ዕቅዱን ለማሳካት ትኩራት የሚሹ ጉደዮች የውስጥ እና የውጭ ስትራቴጂክ አጋርነትን ማጠናከር ከአጋር እና ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ በጋራ መንቀሳቀስ ፣ የዳበረ የስራ ባህል ማምጣት ፣ግብርን በፍቃደኝነት የመክፈል ባህል ማሳደግ ፣ ታክስ ከፋዩን በልዩ ልዩ የግንኙነት አግባቦች በማስተማር፣ በመደገፍ እና እዉቅና በመስጠት አብዛኛው ግብር ከፋይ በፈቃደኝነት የታክስ ግዴታውን እንዲወጣ ማስቻል ያስፈልጋልም ተብሏል፡፡

በሌላም በኩል የታክስ ህግ ተገዢነት ባህሪ ለዉጥ ማምጣት ባልቻሉ አካላት ላይ ተመጣጣኝ የህግ ማስከበር ተግባር ተፈፃሚ የሚደረግበት ስርዓት ማበጀት ፣ የታክስ እና የጉምሩክ አስተዳደር ስርዓቱን ዓለም በደረሰበት የመረጃ ቴክኖሎጂ ስርዓት እንዲደገፍ ማድረግ ፣ የዲጂታል የገቢ አስተዳደር ስርዓት ለአገልግሎት ተቀባዩ ግልጽ፣ ቀላል እና ተደራሽ አገልግሎት በመስጠት፣ የህግ ተገዥነትና አስተዳደራዊ ወጪ በመቀነስ እና የተገልጋዩን ዕርካታ በላቀ ደረጃ በማረጋገጥ የተቋሙን ተልዕኮ ለማሳካት እንደሚሰራ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.