Fana: At a Speed of Life!

የገንዘብ ሚኒስቴር እና የዓለም ባንክ የ300 ሚሊየን ዶላር የድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን ለመልሶ ማቋቋሚያ የሚሆን የ300 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር ስምምነት ተፈራረመ።
ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳንና የኤርትራ ዳይሬክተር ኦስማን ዲዮን ጋር ተፈራርመዋል።
የድጋፍ ስምምነቱ በአማራ፣ አፋር፣ ትግራይ፣ ኦሮሚያና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በግጭት ለተጎዱ አካባቢዎች ለመልሶ ግንባታና መልሶ ማቋቋሚያ የሚውል ነው ተብሏል።
ድጋፉ በተመረጡ የግጭት ተጎጂ ወረዳዎች የጤና፣ የትምህርትና የውሃ መሰረት ልማት መዘርጋት ብሎም ለፆታዊ ጥቃት የተጋለጡ ሴቶችን ለመደገፍና መልሶ ለማቋቋም እንደሚውልም ተመላክቷል፡፡
የፌዴራል መንግስት በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት በተያያዘው ዓመት 5 ቢሊየን ብር መመደቡን ያስታወሱት አቶ አሕመድ ሺዴ÷ በቀጣይ በጀት ዓመት ደግሞ 20 ቢሊየን ብር መመደቡን ተናግረዋል።
የዓለም ባንክ ለመልሶ ግንባታ ያደረገው ድጋፍ በጦርነቱ ከደረሰው ውድመት አንፃር ከፍተኛ ባይሆንም ለተጎዱ አካባቢዎች አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ግን ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ባንኩ የዛሬ ወር በኢትዮጵያ በግጭት ምክንያት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት ለተዘጋጀ ፕሮጀክት የሚውል የ300 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ ማፅደቁ የሚታወስ ነው።

በተለይም ድጋፉ የመሰረታዊ አገልግሎት አቅርቦትን ለማሻሸል እና ለዓየር ንብረት ለውጥ የማይበገር መሰረተ ልማት ለመገንባት እና በግጭት የተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎችን እንደሚያስቀድም ነው ባንኩ ያመለከተው።

በአጠቃላይ ድጋፉ ከ5 ሚሊየን የሚበልጡ ሰዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም የባንኩ መረጃ ያመላክታል።

ውጤታማ እና ፈጣን ምላሽ ለመስጠትም በማሰብ የገንዘብ ድጋፉ በፌደራል መንግስት፣ በክልል መንግስታት እና በአካባቢዎቹ በሚንቀሳቀሱ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በኩል እንደሚቀርብም ገልጿል።

 

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.