Fana: At a Speed of Life!

የጉንፋን ሕመም ምንነት፣ የሚከሰትበት ወቅት፣ የሕመሙ ምልክቶች፣ የመተላለፊያ መንገዶች፣ እና የመከላከያ ዘዴዎች

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የጉንፋ ሕመም በተፈጥሮ የላይኛውን የመተንፈሻ የሰውነት ክፍሎች ማለትም አፍንጫን፣ ጎሮሮን እና የአየር መተላለፊያ ባንቧን የሚያጠቃ ተላላፊ ሕመም መሆኑን ጤና ሚኒስቴር በመረጃው አመላክቷል፡፡

ሪኖ ቫይረስ፣ ኮሮና፣ ኢንፍሉዌንዛ እና ፓራ ኢንፍሉዌንዛ ቫይረሶች ደግሞ ለጉንፉን መከሰት ዋና ምክንያቶች መሆናቸውንም ነው የጠቀሰው።

ከተጠቀሱት ቫይረሶችም ለጉንፋን ሕመም መከሰት 50 በመቶ ድርሻውን የሚይዘው ሪኖ ቫይረስ እንደሆነ ነው የተመለከተው፡፡

በደረቅ ንፋሳማ አካባቢዎች እና በክረምት ወራት ደግሞ የአፍንጫ “ሙከስ” ስለሚደርቅ የጉንፋን ሕመም እና ተላላፊነቱ ይጨምራል ነው የተባለው፡፡

በጉንፋን ሕመም የተያዘ ሰው የሚያሳያቸው ምልክቶችም ሳል፣ የጉሮሮ መከርከር፣ ማስነጠስ፣ የአፍንጫ መቅላት ትኩሳት፣ የአፍንጫ ፈሳሽ፣ የመገጣጠሚያ ሕመም፣ ራስ ምታት ናቸው፡፡

በተጨማሪም የጉንፋን ሕመም የጆሮ ኢንፌክሽኖችን እና የሳንባ ምች ሕመምን ጨምሮ ለተለያዩ በባክቴሪያ ለሚከሰቱ ሕመሞች ተጋላጭ ሊያደርግ እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡

የጉንፋን ሕመም ባስ ሲል ታማሚውን ሆስፒታል እስከ ማስገባት እና አልጋ መያዝ ብሎም አልፎ አልፎ እስከ ሞት ሊያስከትል እንደሚችል ተገልጿል፡፡

አስም ፣ የስኳር በሽታ ፣ ካንሰር እና ሌሎች ሥር የሰደዱ በሽታዎች ደግሞ የጉንፋን ሕመምን ሊያባብሱት ይችላሉ፡፡

ሕመሙ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፈውም በቫይረሱ የተጠቃ ሰው በሚያስልበት ወይም በሚያስነጥስበት ጊዜ እንደሆነና በተጨማሪም ሰዎች ቫይረሱ ያረፈበትን የበር እጀታ፣ ጠረጴዛ ወይም በሕመምተኛው የተበከለን ሰው እጅ ከነኩ በኋላ አፋቸውንና አፍንጫቸውን ሲነካኩ ቫይረሱ ለመተላለፍ በሚፈጠርለት ምቹ ሁኔታ ነውም ተብሏል።

የጉንፋን ሕመምን ዘወትር እጅን በውሃ እና በሳሙና በመታጠብ፣ ውሃ እና ሳሙና በማይገኝበት ወቅት ደግሞ የአልኮል ይዘት ያላቸውን የእጅ ማጽጃዎችን በመጠቀም መከላከል እንደሚቻል ተመልክቷል፡፡

አይንን፣ አፍ እና አፍንጫን ከመነካካት መቆጠብ፣ ሲያስነጥሱ እና ሲያስሉ አፍን በክንድ መሸፈን፣ ሕመምተኛው ሶፍት ወይም መሃረብ ከያዘ ሲያስነጥስ እና ሲያስል አፉን በሶፍቱ ወይም በመሃረቡ በመሸፈን ማሳል እና ሶፍቱን ወይም መሃረቡን በአግባቡ በማስወገድ ከዚያም እጁን በመታጠብ ሌሎችን በሕመሙ ከመያዝ እንደሚታደግም መረጃው ያመለክታል፡፡

እንደ ጠረጴዛ፣ ሲንክ፣ የቧንቧ እጀታዎች፣ ስልክ እና እንደ ማብሪያ እና ማጥፊያ ያሉ በዕለት ኑሯችን የምንጠቀምባቸውን በከባቢዎቻችን የሚገኙ ቁሶች በበረኪና ወይም መሠል የጀርም ማጽጃዎች ማጽዳትም የሕመሙን የመተላለፍ ዕድል ያጠበዋል ተብሏል፡፡

የጉንፋን ሕመም የመጀመሪያ ምልክቱ ከመጀመሩ አንድ ቀን በፊት ተላላፊ ሊሆን ይችላል፤ ሕመሙ ከጀመረ ከ 5 እስከ 10 ባሉት ቀናት ደግሞ ሕመምተኛው ቫይረሱን ያስተላልፋል።

አንዳንድ ጊዜ ልጆች በጉንፋን ሕመም ከተያዙ ከ 10 ቀናት በላይ የቫይረሱ አስተላላፊ ሊሆኑ እንደሚችሉም ከጤና ሚኒስቴር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.