Fana: At a Speed of Life!

የግለሰብ መኖሪያ ቤት በመግባት ተሽከርከሪ የዘረፉ ግለሰቦች በእስራት ተቀጡ

 አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 30 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የግለሰብ መኖሪያ ቤት በመግባት ተሽከርከሪ ጭምር ዘርፈዋል በተባሉ ሶስት ግለሰቦች በ18 እና በ20 አመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተወሰነ።
ተከሳሾቹ ተመስገን ማርቆስ፣ ሲሳይ ተሾመ እና ዳንኤል ተዘራ የተባሉ ግለሰቦች ሲሆኑ፥ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32(1) ሀ እና 671 (2)ን በመተላለፍ በዋና ወንጀል አድራጊነት በከባደ ውንብድና ወንጀል ነው የተከሰሱት።
የዐቃቤ ህግ ክስ እንደሚያመላክተው ጥቅምት 5 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አባባ ከተማ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 17 ጤና ጣቢያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከሌሊቱ 9 ሰአት ላይ ካልተያዙ አምስት ግብረ አበሮቻቸው ጋር በመሆን ጩቤና ሽጉጥ እንዲሁም ገጀራ በመያዝ የግል ተበዳይ ከሆኑት የአቶ አሊ ሁሴን መኖሪያ ግቢ ውስጥ የግንብ አጥር ዘለው ገብተዋል።
ወደ ግል ተበዳይ መኝታ ቤት በማቅናትም አቶ አሊ ሁሴንን አስፈራርተው የግለሰቡን አፍ በፕላስቲክ ማሸጋቸውን ዐቃቢ ህግ በክሱ አመላክቷል።
ግለሰቡ ራሳቸውን ለማዳን ሲታገሉ ዘራፊዎቹ የተበዳይ ሁለት አውራ ጣቶቻቸውን በስለት መጉዳታቸውንም አብራርቷል።
በዚህ መልኩ የግለሰቡን ኮድ 3 የሆነ ላንድሮቨር ተሽከርካሪ፣ የባለቤታቸውን የጣት ወርቅ ቀለበት እንዲሁም 2 ሚሊየን 800 ጥሬ ብር በመውሰድ ዝርፊያ መፈጸማቸወን ዐቃቤ ህግ በክሱ አመላክቷል።
ፍርድ ቤቱም ዐቃቤ ህግ ያቀረበውን የሰውና የሰነድ ማስረጃ ከመረመረ በኋላ ተከሳሾቹ እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቶ የነበረ ሲሆን ተከሳሾቹ በተገቢው መልኩ መከላከል አልቻሉም ተብለው ጥፋተኛ ተብለዋል።
በዚህ ዛሬ በዋለው ችሎት ተመስገን ማርቆስ እና ሲሳይ ተሾመ በ18 አመት ጽኑ እስራት እንዲሁም ዳንኤል ተዘራ የተባለው ተከሳሽ በ20 አመት ጽኑ አስራት እንዲቀጡ ተወስኗል።
በውሳኔው ቅር የተሰኘ ተከሳሽ ይግባኝ የማለት መብቱ የተጠበቀ ነው ብሏል ችሎቱ ።
በታሪክ አዱኛ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.