Fana: At a Speed of Life!

የግብጽ እና ሱዳን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሄድ መለስ ፖለቲካ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 14፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) ግብፅ እና ሱዳን አሁንም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ በሚደረገው ድርድር የሄድ መለስ ፖለቲካቸውን ገፍተውበታል።

ፈርዖኖች ዛሬም አሳሳች የውሃ ዲፕሎማሲያቸውን እንደገፉበት ነው። ይህ የካይሮ አካሄድ በሁለት በኩል የሚወነጨፍ ነው።

አንደኛው በአሳሳች ምሁራኖቻቸው እና በመንግስት በኩል የሚካሄድ የሴራ የውሃ ፖለቲካ ጉንጭ አልፋ ሙግት ነው።

ምሁራኖቻቸው በአሳሳች ጥናታዊ ፅሑፎቻቸው በኩል ዓለም አቀፉን ማህብረሰብ ለማሳሳት ሌት ከቀን የሀሰት ዜና ይሰራሉ።

ከእነዚህ ሀሳዊ ጥናቶች መካከል አንዱ በቅርቡ በአሜሪካ የውሃ እና የስነ ህዋ ጥናት ማህበር በኩል ስለ ህዳሴው ግድብ ጠንካራ ጥያቄ ያስነሳው ሀሰተኛ ጥናት ታትሞ እንደነበር ይታወሳል።

ይህን የሀሰት ጥናት ማህበሩ ከድረ ገፁ እንዲያነሳ እና እንዲሰርዝ በትውልደ ኢትዮጵያውያን ምሁራን በኩል ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል።

ጉዳዩን በቅርበት ሲከታተሉ ከነበሩት ትውልደ ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ የሆኑት በደቡብ ፍሎሪዳ ዩኒቨርሲቲ የውሃ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ጥሩሰው አሰፋ ናቸው።

የግብፅ ተደራዳሪዎችን ሀሰተኛ መከራከሪያ ብቻ ሳይሆን የአሳሳች ምሁራኖቻቸውን ሀሳብም በማስረጃ መቃወም ይገባል ነው የሚሉት።

ቀዳሚው ፈጣን ምላሽ መስጠት እና ዓለም አቀፉ ማህብረሰብ ከጥናቱ ይልቅ በጥናቱ የተቃውሞ ሃሳብ ላይ እንዲያተኩር ማድረግ እና ሌሎችንም ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ይረዳል፡፡

ሁለተኛው የሀሰተኛ ምሁራን ስራዎችን ማጋለጫ መንገድ ከአሁን በፊት የሰሯቸውን ጥናቶች እና አሁን ያቀረቡትን ጥናት ተቃርኖ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በበይነ መረብ ማሳወቅ ይገባል ባይ ናቸው፡፡

ፈርዖኖቹ ኢትዮጵያ ጠንከር ብላ ስትታይ ድርድር ደከም ብላ ስትታይ ወታደራዊ ሃይልን እንደማስፈራሪያ ሲመርጡ ይስተዋላል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ዶክተር ተፈሪ መኮንን የፈርዖኖች የትናንት ጉዞ ዓባይን መጠቀም በማያስችል ምጣኔ ሀብታዊ ምህዋር ውስጥ እንድንሽከረከር የማድረግ የዲፕሎማሲ አካሄድ ነበር ይላሉ።

በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ እና በብሉ ናይል የውሃ ጥናት ማዕከል ተመራማሪው ውብ እግዜር ፈረደ ግብፅ የዛሬ 20 ዓመት በናይል ጉዳይ ላይ ያተኮረ ጉባኤ አካሂዳ እንደነበር ያስታውሳሉ።

የዓረብ ውሃ ጉባኤ የሚል ስያሜ የያዘው ጉባኤ ግን የአሳሳች ዲፕሎማሲዋ ምን ያህል እንደተጓዘ የሚያሳይ ነበር ነው የሚሉት።
በዚህ ጉባዔ ላይ ናይል እንዴት ዓረባዊ ወንዝ እንደሆነ እና በቀጣይ በሲናይ በርሃ እስከ ዓረብ ሀገሮች ድረስ የተሻገረ የልማት ቀጠና እንደሚዘረጋበት የተብራራበት ነበርም ይላሉ።

የወቅቱ ፕሬዚዳንት የነበሩት ሆስኒ ሙባረክ አዲሱ የናይል ሸለቆ ልማት በሚል ግዙፍ ፕሮጀክት ይፋ አደረጉ።

እርሳቸውም ሆኑ ተተኪያቸው መሃመድ ሙርሲም በመጡበት ታህሪር አደባባይ ተባረዋል፤ የአሁኑ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ ሲተኩም የሙባረክን ፕሮጀክት በአዲስ መልክ አፋጠኑት ።

ከንጉሶች እና ኤሚሮች ረብጣ ቢሊየን ዶላር እየተበደሩ በስማቸው የቦይ ስያሜም ሰይመውላቸዋል።

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲው ውብእግዜር ፈረደ እንደሚናገሩት ይህ ዓባይን የዓረብ ጉዳይ የማድረግ ሴራ ነው።

በሄድ መለስ የታጀበው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ድርድር አሁንም በወጣ ገባ ሁነት ታጅቦ እንደቀጠለ ነው።

ሰሞኑን የሱዳን ሰዎች አዲስ መንፈስ ከሌለበት አንሳተፍም ማለታቸው ዛሬም የዓባይ ፖለቲካ ከአሳሳቹ የካይሮ ዲፕሎማሲ ራዳር ውጭ እንዳልሆነ ማሳያም ነው።

የሱዳንን ወቅታዊ የፖለቲካ ሽግግር በቅርበት የሚያጠኑ ምሁራን እንደሚናገሩት ካርቱም ሁለት የፋይናንስ ቀውስ እና በሁለት እግሩ ያልቆመው የፖለቲካ ሽግግር ትልቅ ፈተናዎቿ ናቸው።

እነዚህ ሁነቶች በግድቡ ዙሪያ አንድ አቋም እንዳትይዝ እንዲሳናት እያደረገ መሆኑን ይናገራሉ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው የህግ ምሁር ዶክተር ደረጀ ዘለቀ ከአሁን በኋላ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ የሚደረግ ድርድር እነዚህን ነጥቦች ታሳቢ ማድረግ አለበት ባይ ናቸው።

የካይሮ ሰዎች በየጊዜው በህዳሴው ግድብ ዙሪያ አፍራሽ መግለጫ ሲሰጡ ተደምጧል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው የውሃ ፖለቲካ ተመራማሪ እና የአፍሪካ ጥናት ትምህርት ክፍል ባልደረባው ፕሮፌሰር ተስፋዬ ታፈሰ እንደሚናገሩት ኢትዮጵያ ቀጥታ ካይሮ ሀያል እርምጃ ትወስዳለች ከሚለው ይልቅ ሁልጊዜም የግብጽን አምስተኛ ረድፍ በጥንቃቄ መመከት ይገባልም ነው የሚሉት።

የህዳሴው ግድብ በእርግጥ ኤሌክትሪክ ሃይል ከማመንጨት እና ብሄራዊ ሀብትን ከመጠቀም ባለፈ ምዕባውያን ከብዙ ፍላጎቶቻቸው ጋር አብረው የሚፈፅሙትን የእርዳታ ዲፕሎማሲ ማቅለያም ጭምር ነው።

ፕሮፌሰር ተስፋዬ ይህ ጉዳይ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባው አስምረውበታልት፤ ባለፈው ተሰናባቹ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እርዳታ አቆማለሁ ፉከራን እንደማሳያ በማቅረብ
ተመራጩ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን እና አስተዳደራቸው በካይሮ አሳሳች ዲፕሎማሲ ዳግም እንዳይሸበቡ አዲስ አበባ ከወዲሁ ጠንካራ ስራ መስራት እንዳለባት የሚመክሩ ባለሙያዎች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም።

በስላባት ማናዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.