Fana: At a Speed of Life!

የጎርጎራ ፕሮጀክት መጀመር የአካባቢውን የዘመናት የልማት ጥያቄን የመለሰ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 29 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የጎርጎራ ገበታ ለሀገር ፕሮጀክት መጀመር ለዘመናት ሲነሳ ለነበረው የልማት ጥያቄ በተግባር ምላሽ የሰጠ መሆኑን የጎርጎራ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ አለባቸው ስሜ ለኢዜአ እንዳሉት÷በገበታ ለሀገር  የታቀፈችው የጎርጎራ ፕሮጀክት መጀመር የከተማዋን ትንሳኤ ዳግም ያበሰረ ነው፡፡

በተፈጥሮ ሀብት የታደለችው ጎርጎራ ለዘመናት አስታዋሽ አጥታ ህዝቡ በድህነት አዙሪት ውስጥ  መቆየቱን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጎርጎራ እንድትለማ የወጠኑትን ታላቅ የልማት አጀንዳ ካበሰሩበት ማግስት ጀምሮ የህዝቡ የልማትና የእድገት ተስፋ ዳግም እንዲለመልም ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

ሌላው የአካባቢው ነዋሪ አቶ ጫቅሉ በበኩላቸው÷ ጎርጎራ ባለፈው ሥርዓት በልማት ተረስታ በመቆየቷ በጉያዋ ያሉትን የልማት ጸጋዎች ለህዝብ ጥቅም ሳይውሉ መቆየታቸውን አውስተዋል።

በኢንቨስትመንት ስም ቦታ ወስደው ለረጅም ዓመታት አጥረው ያስቀመጡ ባለሀብቶችም የከተማዋን የልማት ትንሳኤ ሳይሆን ውድቀት ሲያመቻቹ የቆዩ ነበሩ ብለዋል፡፡

ዛሬ ትንሳኤዋን የሚያበስር የሀገር መሪ አግኝታ የገበታ ለሀገር ተጠቃሚ ለመሆን ፕሮጀክቱ በይፋ በመጀመሩ የዘመናት የልማት ጥያቄያችን ምላሽ ያገኘበት ልዩ ቀን ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የጎርጎራ ገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ለአካባቢው ወጣቶች ሰፊ የስራ እድል ይዞ መጥቷል ያለው ደግሞ ወጣት መንግስቱ አይናለም ነው፡፡

በከተማው ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ከቤተሰብ ጠባቂ በመሆን ቤት ውስጥ የተቀመጡ በርካታ ወጣቶች መኖራቸውን የጠቆመው ወጣት መንግስቱ ፕሮጀክቱ የወጣቱን የማደግና የመለወጥ ፍላጎት ያነቃቃ ነው ብሏል፡፡

የምዕራብ ደንቢያ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ይርጋ አይቸው የጎርጎራ ገበታ ለሀገር ፕሮጀክት በአጭር ጊዜ 134 ባለሀብቶችን ወደ አካባቢው መሳብ ችሏል ብለዋል፡፡

አስተዳደሩ በከተማው መዋዕለ ንዋያቸውን ተጠቅመው በልማቱ ለሚሳተፍ  የፕሮጀክት ጥናት እና የግንባታ ቦታ ጥያቄ ላቀረቡ ባለሀብቶች 300 ሄክታር የኢንቨስትመንት ቦታ ማዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

በጎርጎራ ከተማ በአንድ ቢሊዮን ብር ወጪ ለሚገነባው ፕሮጀክት ዶክተር አብይ አህመድ ትናንት የመሰረት ድንጋይ በማስቀመጥ ግንባታውን በይፋ ማስጀመራቸውን ይታወሳል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.