Fana: At a Speed of Life!

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የደቡብ አፍሪካ ጉብኝት የሀገራቱን ግንኙነት ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት እንደሚያሸጋግር ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በደቡብ አፍሪካ የሚያደርጉት ይፋዊ ጉብኝት የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት እንደሚያሸጋግረው በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም ተናገሩ።

አምባሳደሩ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በስልክ በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት፥ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት እንደሚያጠናክረው ይጠበቃል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ግብዣ ከነገ ጀምሮ በሀገሪቱ የሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ያደርጋሉ።

አምባሳደሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉብኝታቸው በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ በመሪዎች ደረጃ እና ከተለያዩ የሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ይወያያሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

በተጨማሪም በደቡብ አፍሪካ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጋር እንደሚወያዩም አምባሳደር ሽፈራው አንስተዋል።

በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች የደቡብ አፍሪካ መንግስት ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጥ ጥረት ያደርጋሉም ነው ያሉት።

አምባሳደሩ አክለውም ጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አሕመድ በስቴዲየም ከህዝቡ ጋር እንዲገናኙ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

በሀይለየሱስ መኮንን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.