Fana: At a Speed of Life!

የጤና ሚኒስቴር ኮቪድ 19ን ለመከላከልና መሰረታዊ የጤና አገልግሎቶችን ለማጠናከር የሚያግዙ ቁሳቁሶች ድጋፍ ተረከበ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የጤና ሚኒስቴር ኮቪድ 19ን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲሁም መሰረታዊ የጤና አገልግሎቶችን ለማጠናከር የሚያግዙ ቁሳቁሶች ድጋፍ ተረክቧል።

ድጋፉን ያበረከቱትም ፓዝ፣ ዩ ኤስ አይ ዲ የግል ጤና ሴክተር ፕሮጀክት እና የብርቅዬ ልጆች መዝናኛ ከተሰኙ ከሶስት የተለያዩ ድርጅቶች መሆናቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ፓዝን በመወከል ድጋፉን ያስረከቡት ወይዘሮ ትርሲት ግርሻው፥ ድርጅታቸው የሴቶች፣ የእናቶችና ህፃናትን ጤና ለመጠበቅ እንደሚሰራ ገልፀው 2 ነጥብ 1 ሚሊየን ብር የሚያወጣ ኮቪድ 19ን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያግዙ የንፅህናና የመከላከያ ቁሳቁሶችን ድጋፍ አስረክበዋል።

ዩ ኤስ አይ ዲ የግል ጤና ሴክተር ፕሮጀክትን በመወከል ድጋፉን ያስረከቡት ዶክተር አስፋወሰን ገብረዮሐንስ በበኩላቸው ፥ 668 ሺህ ብር ካወጣ ከስትራቴጂ ፕላን ህትመት በተጨማሪ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሚያወጣ የቲቢ መመርመሪያና ማከሚያ ግብዓቶችን አስረክበዋል።

የብርቅዬ ልጆች መዝናኛ የፌስቡክ ግሩፕን ወክለው መልዕክት ያስተላለፉትና ድጋፋቸውን ያስረከቡት አርቲስት ደበበ እሸቱ በበኩላቸው፥ “በኛ ግዴለሽነት የጤና ባለሙያዎቻችን እንዳይሞቱብን ቸልተኝነትን እናስወግድ፤ እንጠንቀቅ” የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።

233ሺህ ብር ገደማ የሚያወጣ ድጋፍም አስረክበዋል።

ድጋፉን የተረከቡት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ድጉማ፥ ኮሮና ከትልልቅ ከተማዎች አልፎ ወደ በርካታ ወረዳዎች እየተስፋፋና ለብዙዎች ሞት ምክንያት ከመሆኑም ባለፈ ትምህርት ቤቶች እየተከፈቱ በመሆናቸው ድጋፉ ወሳኝ ነው ብለዋል።

አክለውም ትልቁ መደጋገፍ ጥንቃቄ ማድረግ በመሆኑ ህብረተሰቡ መከላከያ የሆኑትን ንፅህናን መጠበቅ፣ ማስክ ማድረግና ርቀትን መጠበቅ በሃላፊነት ስሜት እንዲተገበሩ አሳስበዋል።

#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.