Fana: At a Speed of Life!

የጥቃቅንና አነስተኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንተርፕራይዞች ምርቶቻቸውን እንዲያሳድጉ የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 5 ፣2013 ( ኤፍ.ቢ.ሲ) የጥቃቅንና አነስተኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንተርፕራይዞች ምርቶቻቸውን የማሳደግ ዓላማ ያለው የገንዘብ ድጋፍ ስምምነት ተደርጓል።

የገንዘብ ድጋፍ ስምምነቱ የተደረገው በኢትዮጵያ ንግድ እና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት፣ ፕሪሳይስ ኢንተርናሽናል ኮንሰልታንትና የፈጠራ ድርጅት እንዲሁም የግሪን ኢትዮጵያ ማኑፋክቸሪንግ ፕሮጀክት ተጠቃሚ ኢንተርፕራይዞች መካከል መሆኑ ተገልጿል።

ስምምነቱን የኢትዮጵያ ንግድ እና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ጸሐፊ አቶ የሱፍ አደምኑር ከፕሮጀክቱ ኢንተርፕራይዞች ጋር ተፈራርመዋል።

ይህ የማበረታቻ ድጋፍ በኢትዮጵያ ያሉ የጥቃቅንና አነስተኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንተርፕራይዞች የተለያዩ ማሻሻያዎችን በማድረግ ምርቶቻቸውን እንዲያሳድጉ የማበረታታት ዓላማ አለው ተብሏል።

በተጨማሪም ድጋፉ በአምራች ዘርፍ ውስጥ የማያቋርጥ አፈጻጸም እና ቀጣይነት ያለው መሻሻል እንዲኖር ያደርጋል ነው የተባለው።

በገንዘብ ድጋፉ ተጠቃሚ የሆኑት በጨርቃ ጨርቅ፣ በቆዳ እና በእጅ ሥራ የተሰማሩ የጥቃቅን እና አነስተኛ አምራች ድርጅቶች እንደሆኑ ተገልጿል።

ድርጅቶቹ የገንዘብ ድጋፍ ስምምነት ያደረጉት ሃብትን በመቆጠብ፣ ከአየርና ከውሃ ብክለት ነጻ በሆነ መንገድ እና ፈጠራን መሰረት ባደረገ መልኩ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ማምረት በመቻላቸው እንደሆነ ተገልጿል።

ስምምነቱን ያደረጉት በጥቃቅን እና አነስተኛ አምራች ድርጅቶች የተሰማሩ 11 ድርጅቶች እንደሆኑ የግሪን ኢትዮጵያ የማኑፋክቸሪንግ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ኽይሩ ሐሰን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ እና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ጸሐፊ አቶ የሱፍ አደምኑር መርሃ- ግብሩ እንዲሳካ ድጋፍ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበው ÷የገንዘብ ድጋፉ ለተፈለገው ዓላማ እንዲውል ኢንተርፕራይዞቹ በትኩረት መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.