Fana: At a Speed of Life!

የጥፋት ሀይሎችን ህግ ፊት ለማቅረብ መንግስት እየሰራ ይገኛል- የሰላም ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 11፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) ህግ ለማስከበርና ፍትህ ለማስፈን ብሎም የጥፋት ሀይሎችን ህግ ፊት ለማቅረብ መንግስት እየሰራ እንደሚገኝ የሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ።

በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ሰላም ወዳዱን ህዝብ ኢላማ ያደረገ ሀብትና ንብረትን ከማውደም አልፎ በንጹሀን የዜጎች ህይወት ዋጋ እያስከፈለን ያለ የጥፋት ቡድኖች ሴራ እዚህም እዚያም እያጋጠመን ይገኛል ብሏል ባወጣው መግለጫ።

በዚህም ልብ ሰባሪ አጋጣሚዎች አጋጥመዋል እያጋጠሙም ይገኛል ነው ያለው።

እነዚህ በውስጥም በውጭም ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ የጥፋት ሀይሎች ሰላምን ለማደፍረስ፣ ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨትና አንድነትን ለመናድ ጥረት እያደረጉ መሆኑን መላው ህዝብ ተገንዝቦ፣ አንድ ሆኖ ከጸጥታ ሀይሉ ጋር በመተባበር ችግሩን ለመፍታት መረባረብ  ያስፈልገናል ሲል ገልጿል።

መንግስት የጸጥታ ችግሮችን ለመቅረፍ ጸጥታ በማደፍረስ ስራ ላይ በተሰማሩ የጥፋት ቡድኖች ላይ ተከታታይ እርምጃ በመውሰድ የህግ የበላይነት ለማረጋገጥና አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን በከፍተኛ ደረጃ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ አስታውቋል።

ቤተሰብንና ወዳጅን እንኳን በአመጸኞች እጅ ይቅርና በተፈጥሮ ግዴታ ማጣት እጅግ ቅስም የሚሰብር ነው ያለው ሚኒስቴሩ ባጋጠመው የጸጥታ መታወክ ሳቢያ ቤተሰቦቻቸውንና ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ላጡ እና ለተጎዱ ወገኖቻችን መጽናናትን ተመኝቷል።

በእስከአሁኑ ሂደት በተለያዩ ክልሎች ያጋጠሙ ችግሮችና በዜጎች ላይ የተፈጸሙ አሰቃቂና አሳዛኝ ጥቃቶችን በተመለከተ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የምርመራ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብሏል።

የተጀመረው ህግን የማስከበር ስራም ተጠናክሮ ይቀጥላል በማለት በመግለጫው ላይ አመልክቷል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፦https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.