Fana: At a Speed of Life!

የጦር መሳሪያ ምዝገባ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 4 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ)ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመከላከል ሲባል የጦር መሳሪያ ምዝገባ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል አስታወቁ፡፡

ኢትዮጵያ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያን ለመቆጣጠርና ለማስተዳደር በወጣው በአዋጅ ላይ የጦር መሳሪያ ያላቸው ዜጎች የጦር መሳሪያቸውን ህጋዊ ለማድርግ በሁለት ዓመት ውስጥ ማስመዝገብ ይኖርባቸዋል።

በመሆኑም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አዋጁን ተፈፃሚ ለማድረግ የፀጥታ አካላትን በማስተባበርና ሌሎችንም ተግባራት በማከናወን ላይ መሆኑን ወይዘሮ ሙፈሪያት ተናግረዋል።

ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ዓለም አቀፍ ሰንሰለቱ የበዛ ወንጀል በመሆኑ በሁሉም የሀገሪቱ ድንበሮች የቁጥጥር ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉንም ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

በሀገሪቱ እስካሁን መሳሪያን የመሸጥና የማከፋፈል ህጋዊ ፈቃድ በሌለበት ሁኔታ መሳሪያን የመያዝ ልምድ በሰፊው እየተስተዋለ ይገኛልም ነው ያሉት።

መንግስት የችግሩን አሳሳሲነት በመረዳት ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት የጦር መሳሪያ ምዝገባ ለማካሄድ የሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎችን በማከናወን ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

ሆኖም ምዝገባውን ከማካሄድ አስቀድሞ ከህዝብ ጋር የሚከናወኑ የውይይት መድረኮች መኖራቸውን ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡

በመሳሪያ ዝውውርና ባለቤትነት ላይ ህጋዊ የሆነ መሰረት እንዲኖርና ህገ ወጥ የመሳሪያ ዝውውርን ለመከላከል ሥርዓት ለመዘርጋት ዓለም አቀፍ ተቋማትን ያሳተፈ ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ጌቱ ተክለዮሃንስ እንዳሉት፤ የፀጥታ አካላት ህገ ወጥ የሆኑ ጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመከላከል ጥብቅ የሆነ ቁጥጥር እያደረጉ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ይሁን እንጂ ወንጀሉ ውስብስብ በመሆኑ አሁንም ከገጠር እስከ ከከተማ የዝውውር ሰንሰለት መኖሩን ጠቅሰው÷ህገ ወጥ የጦር ማሳሪያ አገርን የሚጎዳና ህዝቡን ስጋት ላይ የሚጥል በመሆኑ ህግ እንዲተገበር ህዝቡ ከፅጥታ አካሉ ጋር በትብብር እንዲሠራ ጠይቀዋል።

#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.