Fana: At a Speed of Life!

የጦር መሳርያ አስተዳደርና ቁጥጥር ረቂቅ ደንብ ማጠናከሪያ አውደጥናት እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 5፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የጦር መሳርያ አስተዳደርና ቁጥጥር ረቂቅ ደንብ ማጠናከሪያ አውደጥናት በቢሾፍቱ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
በአውደ ጥናቱ ላይ የፌደራል፣ የክልል እና የከተማ አስተዳደር የስራ ኃላፊዎችና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ መሆናቸው ተገልጿል።
አውደጥናቱን በኢፌዲሪ የሰላም ሚኒስቴር የሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አህመድ ሰይድ ተገኝተው የከፈቱ ሲሆን÷ በመልዕክታቸውም ሕገ-ወጥ የሆኑ ቀላል የጦር መሳርያዎች በአፍሪካ ደህንነት እና መረጋጋት ላይ ትልቅ ስጋት ናቸው ብለዋል።
በመሆኑም ሃገራት የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰዱ ይገኛሉ።
ሃገራችን ኢትዮጵያም የጦር መሳሪያቸውን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር እና ለመቀነስ ያለመውን የናይሮቢ ፕሮቶኮል የሕግ ማእቀፍ እ.ኤ.አ. ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ አባል መሆኗን ገልጸዋል።
ነገር ግን ላለፉት 15 ዓመታት አባል መሆን ብትችልም ብሔራዊ የጦር መሳሪያ የሕግ ማእቀፍ ሳይኖራት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ መቆየቷን ገልጸዋል።
መንግስት የጦር መሳሪያ ዝውውር አንዱ የደህንነት እና የሰላም መሸርሸርሪያ ምክንያት መሆኑን በመገንዘብ በጥር ወር 2012 ዓ.ም የጦር መሳሪያ አስተዳደር እና ቁጥጥር አዋጅን አጽቋልም ነው ያሉት።
አዋጁን ተከትሎ የማስፈጸሚያ ረቂቅ ደንቡ በሰላም ሚኒስቴርና በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በጋራ ተዘጋጅቶ የቀረበ ሲሆን ÷የዛሬው መድረክም ተጨማሪ ግብዓት የማሰባሰብና ደንቡን የበለጠ ለማጠናከር ያለመ መሆኑን መግለጻቸውን ከሰላም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.