Fana: At a Speed of Life!

የፀጥታው ምክር ቤት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት፣ ፖለቲካዊ ነጻነት፣ የግዛት እና ሃገራዊ አንድነት እንደሚያከብር አረጋገጠ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 15 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የፀጥታው ምክር ቤት አባላት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት፣ ፖለቲካዊ ነጻነት፣ የግዛት እና ሃገራዊ አንድነት በፅኑ እንደሚያከብር አረጋገጠ።

የተባበሩት መንግስትት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አባላት በኢትዮጵያ በተለይም በትግራይ ክልል ስላለው ሰብአዊ ሁኔታ አስመልክቶ መግለጫ አውጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም መንግስት በትግራይ ክልል ለሚያደርገው የሰብአዊ ድጋፍ እውቅና በመስጠት ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አያይዘውም መንግስት እያደረገ ያለው ድጋፍ ቢቀጥልም በክልሉ ያለው የሰብአዊ ቀውስ አሁንም አሳሳቢ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ምክር ቤቱ ዓለም አቀፉ ተራድኦ ድርጅቶችም የአስቸኳይ ጊዜ ሰብአዊ ድጋፍ መርሆዎችን በተከተለ መንገድ የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲያጠናክሩም ጠይቋል።

አሁን ላይ በትግራይ ክልል ያለው የፀጥታ ችግር ሰብአዊ ድጋፉን በሚፈለገው መጠን ለማቅረብ እንቅፋት መሆኑን ጠቅሶ፥ ክልሉ ወደ ነበረበት እንዲመለስም ጥሪውን አቅርቧል፡፡

አባላቱ በክልሉ አለ የተባለው የሰብአዊ መብት ጥሰት በተለይም ፆታዊ ጉዳይ ጥቃት እንዳሳሰባቸው የገለጹ ሲሆን፥ ከዚህ ጋር ተያይዞ ጥፋተኞችን ለህግ ለማቅረብ ምርምራ እንዲደረግም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ከተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽን ጋር በመሆን በክልሉ ተፈፅመዋል የተባሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ለማጣራት የጀመሩትን እንቅስቃሴ በበጎ እንደሚመለከቱትም አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የሰብአዊ መብት ኮሚሽን እያበረከተ ያለውን አስተዋፅኦ ምክር ቤቱ እውቅና የሰጡ ሲሆን፥ ሂደቱ ዓለም አቀፍ ህግጋትን የተከተለ እንዲሆንም ጥሪ አቅርበዋል።

የአፍሪካ ሕብረት እና የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) በቀጠናው ሰላም ለማስፈን ለሚያደርጉት እንቅስቃሴም ያላቸውን ድጋፍ ገልጸዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.