Fana: At a Speed of Life!

የፀጥታ ኃይሎች ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በታች የሆነን ገንዘብ በህገ ወጥነት መያዝ እንደሌለባቸው ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የፀጥታ ኃይሎች ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በታች የሆነን ገንዘብ በህገ ወጥነት መያዝ እንደሌለባቸው ተገለፀ።

የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ እና የብሄራዊ ባንክ ገዢ ዶክተር ይናገር ደሴ በዛሬው እለት አዲሱን የብር ኖት ለውጥ ተከትሎ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫው ላይም የብሔራዊ ባንክ ገዢ ዶክተር ይናገር ደሴ፥ ከብር ኖት ለውጡ ጋር በተያያዘ የተወሰነ ውዥንብር መፈጠሩን ገልጸዋል።

በዚህም የፀጥታ ሀይሎች በመቶ ሺዎች ይዘው የሚንቀሳቀሱ ሰዎችን እየያዙ መሆኑን እና ይህም ተገቢ አለመሆኑን ጠቅሰው እስከ 1 ነጥብ 5 ሚልየን ብር ያላቸው ሰዎች ያለመሳቀቅ መንቀሳቀስ ይችላሉ ብለዋል።

ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ መያዝን የሚከለክለው መመሪያ እንደ ነዳጅ ማደያ እና ሌሎች ከፍተኛ ሽያጭ የሚያከናውኑ ተቋማትን እንደማይመለከትም ተጠቅሷል።

ነገር ግን ባለሀብቶች በእነዚህ ተቋማት በኩል ገንዘባቸውን በዚህ መንገድ እናስገባለን ብለው ከሞከሩ የንግድ ተቋማቱ የሽያጭ ታሪካቸው ክትትል ስለሚደረግበት እንዳይሞክሩትም አሳስበዋል።

አንዳንድ ግለሰቦች መመሪያው ባንክ ብቻን የሚመለከት ነው በሚል በርከት ያለ ገንዘብ በማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት በኩል ለማስገባት ሙከራ እያደረጉ የተገለፀ ሲሆን፥ መመሪያው ለባንኮችም ለማይክሮ ፋይናስ ተቋማትን እኩል የሚያገለግል መሆኑ ተነስቷል።

በተለያዩ ባንኮች ሂሳብ በመክፈት ገንዘብ በትኖ ለማስቀመጥ የሚሞክሩ ካሉም ይህንን የሚቆጣጠር ግብረ ሀይል መቋቋሙ እና ይህንን ተግባር ፈጽሞ በተገኙት ላይ ብራቸውን እስከ መውረስ የሚደርስ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድም ተነስቷል።

እንዲሁም በተለያዩ ሰዎች አማካኝነት ገንዘብ ማስቀመጥ እንዲሁም በሌላ ሰው ስም ገንዘብ ማስገባት እንደማይቻልም በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።

ከአሽከርካሪዎች ጋር በተያያዘም ከጎረቤት ሀገራት በተለይ ከጅቡቲ ጋር በተያያዘ አሽከርካሪዎች ገንዘብ ይዘው ስለሚንቀሳቀሱ፤ ሁሉም ገንዘብ ህገ ወጥ ነው ተብሎ መያዝ እንደሌለበት በመግለጫው ተጠቅሷል።

አሽከርካሪዎች ከሀገር ሲወጡ እስከ 30 ሺህ ብር ይዘው መውጣት እንደሚችሉ፤ ሲገቡ ደግሞ እስከ 10 ሺህ ብር መያዝ የሚችሉ መሆኑም ታውቋል።

ሆኖም ግን በህገ ወጥ መንገድ ብር በተሽከርካሪያቸው ውስጥ ደብቀው ለማስገባት የሚመክሩ ካሉም እንደሚወረስባቸው ተነስቷል።

በትእግስት አብረሃም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.