Fana: At a Speed of Life!

የፅንፈኛው ቡድን የመረጃ ምረዛን ለማክሸፍ እውነታን መሰረት ያደረገ የተቀናጀ ስራ መስራት እንደሚገባ ምሁራን ተናገሩ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 8፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) የፅንፈኛው ቡድን የመረጃ ምረዛን ለማክሸፍ እውነታን መሰረት ያደረገ የተቀናጀ ስራ መስራት እንደሚገባ በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ እና በሩሲያ የወዳጅነት ዩኒቨርሲቲ በምርምር ስራ ላይ የሚገኙ ትውልደ ኢትዮዽያውያን ምሁራን ተናገሩ።
የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ተመራማሪ ፕሮፌሰር አበበ ዘገዬ እና የሩሲያ የወዳጅነት ዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር ዘነበ ክንፉ መንግስት በውጭ ከሚገኙ ትውልደ ኢትዮዽያውያን ምሁራን ጋር ጠንካራ የመረጃ ስርዓት ገንብቶ ብሄራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ በጋራ መስራት ይገባዋል ብለዋል።
በእንግሊዙ ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የእስራኤል እና የአይሁዳውያን ጉዳይ ማዕከል ውስጥ ከፍተኛ የማህብረሰብ ጥናት ተመራማሪው ፕሮፌሰር አበበ ዘገዬ በሚኖሩበት እንግሊዝ እና በሌሎች የአውሮፓ አካባቢዎች ስለ ኢትዮዽያ ያለው የመረጃ ፍስት የፅንፈኛው ቡድን የመረጃ ምረዛ ተፅእኖ ያረፈበት እና ህግ የማስከበሩ ዘመቻም በተቃራኒ እየተመነዘረ ሌላ ስም እየተሰጠው የኢትዮጵያን ስም የሚያጎድፍ ነው ብለዋል።
ፕሮፌሰሩ ለዚህ ውጤት ምክንያት ያሉት የፅንፈኛው ቡድን የዓመታት የሴራ ዲፕሎማሲ መሆኑንም አውስተዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታትም የዚህ ቡድን የመረጃ እንደራሴዎች ከቡድኑ በሚሰጣቸው ገንዘብ ከፍተኛ የሆነ የሀሰት መረጃ ሲያሰራጩ መቆየታቸውንና አሁን ላይም የሀሰት መረጃ ስርጭታቸውን እያስፋፉ መሆኑን አንስተዋል።
በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ምሁራንን ያካተተ ፣ በሀገር ቤት የሚገኙ የጂኦ ፖለቲካ ተከታታዮችን የጨመረና በዋናነት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ድጋፍ የሚደረግለት ጠንካራ የውጭ ጉዳይ መማክርትን ማቋቋምም ቀዳሚው መፍትሄ ሊሆን ይገባልም ነው ያሉት።
በተጨማሪም ኤምባሲዎች እና ቆንስላ ፅህፈት ቤቶችም ለወቅታዊው የህግ ማስከበር ዘመቻ ብቻ ሳይሆን ለዓባይ እና ለሌሎች የጂኦ ፖለቲካ ጉዳዮች የዲፕሎማሲ ስራ የሚያግዝ የመረጃ ስርዓት መፍጠር እንደሚገባቸው ጠቁመዋል።
ከዚህ ባለፈም ኢትዮጵያን በውጭ ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ የሚያሳዩ ጥናት እና ምርምሮች እንዲሁም መፅሐፍ መሰራጨት እንዳለባቸው አንስተዋል፤ ሃላፊነቱ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን መሆኑን በመጥቀስ።
በሩሲያ የወዳጅነት ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነት እና የጋዜጠኝነት ትምህርት መምህር እና በሩሲያ የአፍሪካ ዳያስፖራዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ዘነበ ክንፉ በበኩላቸው÷ የፅንፈኛው ቡድን የሀሰት ውንጀላ እና ህግ የማስከበሩን ዘመቻ ወደ እርስ በእርስ ጦርነት ቀይሮ የማቅረብ የመገናኛ ብዙሃን ዘመቻ በምስራቅ አውሮፓውያን ተቀባይነት እያገኘ እንዳልሆነ ጠቅሰዋል።
አሁንም የቡድኑ እንደራሴዎች የሀሰት መረጃዎችን እያሰራጩት ያለው ምዕራብ አውሮፓ አካባቢ ባሉ ታላላቅ ሀገራት ጉያ ውስጥ በመሆንና ቡድኑ ለዓመታት ከኢትዮጵያ እየዘረፈ ባሸሸው ገንዘብ የተደለሉ ሰዎች በኩል ነው ብለዋል።
ፕሮፌሰር ዘነበ መንግስት በውጭ ሀገራት ተቀምጠው የኢትዮጵያን ስም የሚያጠለሹ የፅንፈኛው ቡድን ወኪሎች ላይ ዓለም አቀፍ ህግን መሰረት ያደረገ እርምጃ መወሰድ እንዳለበትም አውስተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም በሀሰት መረጃ አደጋ ላይ የሚጥሉ እና የፅንፈኛውን ቡድን የሀሰት መረጃ በማሰራጨት ላይ የተጠመዱ ድርጅቶች እና ግለሰቦች በአፍሪካ ተቀባይነት እንዳይኖራቸው ማድረግ ይገባልም ነው ያሉት።
ምሁራኑ በዲፕሎማሲው ዓለም የአዲስ አበባ ሚና ከእሳት ማጥፋት ያለፈ እንዲሆን በቀጥታ በርካታ ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት የተለያዩ የምክረ ሀሳብ አፍላቂ ተቋማት እንዲቋቋሙ መንግስት ድጋፍ ማድረግ እንዳለበትም ሃሳብ ሰንዝረዋል።
በስላባት ማናዬ
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.