Fana: At a Speed of Life!

የፋና ላምሮት የድምጻውያን የአሸናፊዎች አሸናፊ ውድድር በመቅደስ ግርማ አሸናፊነት ተጠናቋል

አዲስ አበባ፣ መስከረም 17፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ለ11 ተከታታይ ዙሮች ሲካሄድ በቆየው የፋና ላምሮት የድምጻውያን የአሸናፊዎች አሸናፊ ውድድር በመቅደስ ግርማ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
 
መቅደስ ግርማ የፋና ላምሮት የአሸናፊዎች አሸናፊ የፍጻሜ ውድድርን በማሸነፏ የ500 ሺህ ብር እና የዋንጫ ተሸላሚ ሆናለች፡፡
 
ውድድሩ ከጅምሩ ጀምሮ በፍጻሜው የ500 ሺህ ብር ሽልማት እንደያዘ ነበር የሚታወቀው፡፡
 
የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈጻሚ አድማሱ ዳምጠው ሁለተኛ ለወጣው ተወዳዳሪ 200 ሺህ ብር ሦስተኛ በመሆን ላጠናቀቀው ዮናታን ንብረት ደግሞ የ100 ሺህ ብር ሽልማት ሳይጠበቅ አበርክተዋል፡፡
 
በፍጻሜው ኤልያስ ተክለኃይማኖት 2ኛ፣ ዮናታን ንብረት 3ኛ፣ ግዛቸው ሙላት 4ኛ፣ ሰለሞን ጥጋቤ 5ኛ፣ ኤልያስ ተሾመ 6ኛ በመሆን ውድድራቸውን አጠናቀዋል፡፡
 
ስለ አባይ ባዜሙት ዜማ ሦስት ተወዳዳሪዎች እኩል ነጥብ ያመጡ ሲሆን በዳኛው ምርጫ ኤልያስ ተክለሃይማኖት ተመርጧል፡፡
 
ፋና ላምሮች ለ10 ተከታታይ ዙሮች የተካሄደ ሲሆን ዛሬ ለ11ኛ ጊዜ ነው የተካሄደው፡፡
 
በዛሬው የፍጻሜ ውድድር መቅደስ ግርማ፣ ዮናታን ንብረት፣ ግዛቸው ሙላቱ፣ ኤልያስ ተሾመ፣ ኤልያስ ተክለኃይማኖት፣ እና ሰለሞን ጥጋቡ ተሳትፈዋል፡፡
 
የፍጻሜው ውድድር በሚካሄድበት ወቅት የተለያዩ እንግዶች ታድመዋል፡፡
 
አርቲስት ጎሳዬ ተስፋዬ የፕሮግራሙ የክብር እንግዳ በመሆን ተገኝቷል፡፡
 
ጎሳዬ ተስፋዬ የፋና ብሮድካስቲንግ የክብርና የምስጋና ተሸላሚ ሆኗል፡፡
 
የፍጻሜ ውድድሩ ላይ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈጻሚ አድማሱ ዳምጠው የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል፡፡
 
በንግግራቸውም ለመስቀል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
 
ለተወዳዳሪዎችም እዚህ ድረስ መድረስ በመቻላቸው እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል፡፡
 
ፋና ላምሮት በቴሌቪዥን ከሚተላለፉ ፕሮግራሞች መካከል ሙያና ሙያተኛን ከሚያገናኙ መካከል ዋነኛው ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
 
ዋና ስራ አስፈጻሚውም የማይነጥፍ ስኬት እንዲኖራችሁ ጥበብን አክብሯት ሲሉ ለተወዳዳሪ ድምጻውያን መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
 
ዋና ስራ አስፈጻሚውም ፋና ብሮድካስቲንግ ወቅታዊና አዝናኝ በመረጃ የበለጸገ ማህበረሰብ ለመፍጠር ይተጋል ሲሉ ንግግር አድርገዋል፡፡
 
ሩብ ከፍለዘመን ያሳለፈው ፋና ብሮድካስቲንግ ተወዳጅነት ያላቸው አዳዲስ ፕሮግራሞችንም በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡
 
በተጨማሪም ከጥቅምት ጀምሮ በቴሌቪዥን የአረብኛ ፕሮግራም እንደሚጀምር ጠቅሰዋል፡፡
 
በንግግራቸው ለዳኞች፣ አጭር መልዕክት በመላክ ተሳትፎ ላደረጉ ተመልካቾች ከፋና ብሮድካስቲንግ ጋር አብረው ለሚሰሩ ደምበኞች ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
 
በቀጣይ ምዕራፍ አብረን በመስራት የላቀ ፍሬያማ ዘመን እናመጣለን ብለዋል፡፡
 
ዋና ስራ አስፈጻሚው በውድድሩ መጠናቀቂያ ለሦስቱም ዳኞች ለሙዚቀኛ ብሌን ዮሴፍ፣ ለአቤል ጳውሎስ እና ለአማኑኤል ይልማ ሰርተፊኬት አበርክተዋል፡፡
 
እንዲሁም የፍጻሜ ውድድሩ ተጋባዥ ለነበረው የዜማ ባለሙያ አበበ ብርሃኔ፣ ለፕሮግራሙ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ላደረገው ሚካኤል መኮንን፣ መሸጋገሪያ ሙዚቃውን ለሰራው ታደለ ፈለቀ ለዛየን ባንድ፣ ለኮከብ ባንድ፣ ለሜካፕ፣ ለመብራት ባለሙያዎች የምስጋና ሰርተፍኬት ተበርክቷል፡፡
 
በአብርሃም ፈቀደ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.