Fana: At a Speed of Life!

የፌደራል ፍርድ ቤቶች ለተጨማሪ ቀናት በከፊል ዝግ ሆነው ይቆያሉ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 29 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራል ፍርድ ቤቶች ለተጨማሪ 30 የስራ ቀናት በከፊል ዝግ ሆነው እንደሚቆዩ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታወቀ።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመግታት የፌደራል ፍርድ ቤቶች ከመጋቢት 10 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ግንቦት 30 ቀን 2012 ዓ.ም በከፊል ዝግ ሆነው እንዲቆዩና አስቸኳይነት ያላቸውን ጉዳዮች ብቻ በተረኛ ችሎት እንዲመለከቱ መደረጉ ይታወሳል።

ፍርድ ቤቱ ለጣቢያቸን በላከው መግለጫ የወረርሽኙ ስርጭት እየተስፋፋ፣ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረና የስርጭት አድማሱም እየሰፋ መምጣቱን የጤና ጥብቃ ሚኒስቴር ከሚያወጣቸው መረጃዎች መረዳት መቻሉን ጠቅሷል።

የዳኝነት አገልግሎት ለማግኘት ከክልሎች፣ ከአዲስ አበባና ከድሬዳዋ ከተሞች ወደ ፍርድ ቤቶች የሚመጡ ባለጉዳዮች ቁጥራቸው በርካታ በመሆኑና የእነዚህ ባለጉዳዮች ለቫይረሱ ስርጭት ያላቸውን ተጋላጭነት ለመቀነስ እንዲሁም ዳኞችና ድጋፍ ሰጭ ሰራተኞች ደህንነታቸው በተጠበቀ ሁኔታ ስራቸውን እንዲያከናውኑ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን በማመን የፌደራል ፍርድ ቤቶች ከሰኔ 1 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሀምሌ 10 ቀን 2012 ዓ.ም ለተጨማሪ ቀናት በከፊል ዝግ ሆነው እንዲቆዩ መወሰኑን ገልጿል።

ፍርድ ቤቶች ዝግ ሆነው በሚቆዩበት ጊዜ በተረኛ ችሎት እንዲታዩ ከተለዩት ጉዳዮች በተጨማሪ አነስተኛ የተገልጋይ ቁጥር ያላቸው ሌሎች የዳኝነት አገልግሎት ሊሰጥባቸው የሚችሉ የጉዳዮችን በመለየት አገልግሎቱን በየጊዜው ቀስ በቀስ ለባለ ጉዳዮች ክፍት እየተደረገ እንዲሄድ ይደረጋልም ነው ያለው።

በእነዚህ ጊዜያትም ከሰኔ 30 ቀን 2011 ዓ.ም በፊት የተከፈቱ ውዝፍ ይግባኝ መዝገቦችን ለመወሰን በችሎት ባለ ጉዳዮችን የመስማት አስፈላጊነት የታመኑባቸው ጉዳዮች ተለይተው ውሳኔ እንዲሰጣቸው ይደረጋል።

የወንጀል ይግባኝ ጉዳዮችን በተመለከተ ከማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ጋር የቪዲዮ ኮንፈረንስ መርሃ ግብር በማዘጋጀት ተከራካሪ ወገኖች ይሰማሉ፥ እንደየ ሁኔታው ከባለ ጉዳዮች ጋር በመነጋገር የቃል ክርክራቸውን በጽሁፍ የሚያቀርቡ ሲሆን ውሳኔ ያገኛሉ።

የፍታ ብሔር ይግባኝ ጉዳዮችን በተመለከተ ባለ ጉዳዮችን መስማት አስፈላጊነቱ በዳኞች ከታመነባቸው ጉዳዮች ውጭ የሆኑ መዛግብት እልባት እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡

አስቸኳይ በሆኑ ጉዳዮች በተረኛ ችሎት የተሰጠውን ትዕዛዝ፣ ብይን እና ውሳኔ መሰረት በማድረግ የሚቀርቡ የይግባኝ ጉዳዮች በአፋጣኝ እልባት ያገኛሉ።

አስቸኳነት ያላቸው ጉዳዮች ማለትም ከህጻናት ቀለብና አስተዳደግ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮች፣ የዋስትና ጉዳይ፣ የአሰሪና ሰራተኞች ጉዳይ፣ በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈጸሙ የቤት ውስጥ ጥቃቶች እና ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማስፈጸሚያ መመሪያ ወይም ደንብ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ይሆናሉ።

የፌደራልና የክልል ጉዳዮች ውሳኔን መሰረት በማድረግ ተከፍተው በሂደት ላይ የነበሩ የአፈጻጸም ጉዳዮች የስራና አፈጻጸም አቅጣጫ እስከሚሰጥባቸው ጊዜ ድረስ በደረሱበት ደረጃ ቆመው ይቆያሉ።

በየደረጃው ባሉ ፍርድ ቤቶች ተዘጋጅቶ በሚገለጸው መርሃ ግብር መሰረት የውሳኔ፣ የትዕዛዝ፣ የብይንና የመዝገብ ግልባጭ የመስጠት ተግባር ይከናወናል።

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ስርጭት ለመከላከል ፍርድ ቤቶች በከፊል ዝግ በሆኑባቸው ጊዜያት ወደ ፍርድ ቤቶቹ ቅጥር ጊቢ የሚገቡና የሚስተናገዱት ባለጉዳዮቹ ብቻ ይሆናሉ ተብሏል።

ባለጉዳዮች ለአገልግሎት ወደ ፍርድ ቤት ሲመጡም የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል መልበስ እንዲሁም በመግቢያ በር ላይ በተዘጋጀ እጅ መታጠቢያ እጃቸውን መታጠብ የእርስ በእርስ ርቀታቸውን ጠብቀው እንዲስተናገዱ ይደረጋልም ነው የተባለው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.