Fana: At a Speed of Life!

ከፖለቲካ ፓርቲዎች ገለልተኛ ሆኖ ከሰንደቅ አላማና መለዮ ጋር በመርህ የሚሰራ ሰራዊት ለመገንባት የተጀመረው ሪፎርም ተጠናክሮ ይቀጥላል – ጠ/ሚ ዐቢይ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 20 ፣2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከፖለቲካ ፓርቲዎች ገለልተኛ ሆኖ ራሱን ከሰንደቅ አላማና መለዮ ጋር ሁልጊዜ በመርህ የሚሰራ ሰራዊት ለመገንባት የተጀመረው ሪፎርም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የፌደራል ፖሊስ ሰራዊት ከራስ በላይ ለህዝብና ለሀገር በሚል መሪ ቃል ባካሄደው ክብረ በዓል ላይ ባደረጉት ንግግር ÷ የተጀመረውን የሪፎርም ስራ ለማጠናከር ዛሬ የታየው ትርኢት እና የፌደራል ፖሊስ እየፈጠረ ያለው አቅም ከፍተኛ ኩራትና ጉልበት ሆኗል ብለዋል፡፡
የፖሊስ ሰራዊት ኢትዮጵያውያን ወጥተው እንዲገቡ እና ነግደው እንዲያተርፉ እና መትጋት እንዲችሉ የራሱን ሕይወት እና ጊዜ ሰውቶ ለሀገር የቆመ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ሰራዊቱ ደስታና ሀዘን ሳይበግረው በማንኛም ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ትኩረቱ ሁልጊዜ ኢትዮጵያና ህዝቦቿን መታደግ እንዲችል እንዲሁም ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የተውጣጣና ኢትዮጵያን የሚጠብቅ እንዲሆን መንግስት እንደሚሰራም አንስተዋል፡፡
ሰራዊት ስናንቀላፋ የማይተኛ ስንዝናና የማይዝናና የበዓላት ጊዜውን ህዝብን በመጠበቅ የሚያከብር ሲሆን÷ ሲሰራ የማናመሰግነው ሲያጠፋ ግን የምንወቅሰው ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
የራሱን ፍላጎትና መሻት ትቶ ህዝቡ በዓል እንዲያከብርና በሰለላም እንዲተኛ ኢትዮጵያ ሰላም እንድትሆን ለሚያደርገው ሁለንተናዊ ጥረት የፌደራል መንግስትም ሁሌም ከጎኑ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
ለዚህም መንግስት የተጀመረውን ለውጥ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ላረጋገጥላችሁ እወዳለሁ ብለዋል በንግግራቸው፡፡
ስለሆነም ይህ ፖሊስ እንደ ህግ አስከባሪ ህግን ጠንቅቆ የሚያውቅ እንደ ወንጀለኛ መርማሪ የወንጀል ምርመራ ክህሎት ያለው፣ እንደ ሰራዊት ወታደራዊ ብቃት ያለውና እንደ አድማ በታኝ የተሟላ ተክለ ሰውነት ያለው፣ እንደ ደህንነነት ተቋም መረጃ መሰብሰብና መተንተን የሚችል እንዲሆን እንዲሁም ዘመኑን መዋጀት እንዲችል የቴክኖሎጂ ብቃትና ግንዛቤ ያለው ዘመናዊ ሰራዊት እንዲሆን ይሰራልም ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ ለማንም ጠላት ሸብረክ ሳትል የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞ አጠናክራ እንድትቀጥል ለራሱ የኩራት ለአካባቢው ሀገራት ደግሞ የብቃት ምንጭ የሆነ ሰራዊት ለመገንባት የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አውስተዋል፡፡
የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው የተጀመረው ተቋማዊ ለውጥ የቅርጽ ብቻ ሳይሆን ለበርካታ አመታት ሳይመለሱ የነበሩ ጥያቄዎችን ለማስተካከል የሚያስችል የይዘት ለውጥ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
የፌደራል መንግሥት ከሚያከናውናቸው ታላላቅ ሥራዎች መካካል አንዱ ዘመናዊ የፖሊስ አገልግሎት መስጠት የሚችል ተቋምና የፖሊስ ሠራዊት መገንባት መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
ፖሊስ የአንድ ሀገር ሕዝብ ሕልውና እውን የመሆን ኃላፊነትን መወጣት የሚችለው በአስተሳሰብ፣ በአወቃቀርና በአሠራር ከሕዝብ ጋር ተቀናጅቶ ሲሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.