Fana: At a Speed of Life!

የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች በመተከል ዞን የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት በሚቻልበት ሁኔታ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች በመተከል ዞን ቡለን ወረዳ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት በሚቻልበት ሁኔታ ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት አድርገዋል።

ውይይቱ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ቡለን ወረዳ የተፈጠረውን ችግር ከመሰረቱ ለመፍታት ጉዳዩ የሚመለከታቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር በግልገል በለስ ከተማ መደረጉን መተከል ዞን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።

በውይይቱ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪሀት ካሚል፣ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻዲሊ ሀሰን፣ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ፣ የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብናልፍ አንዷለም እና ሌሎች የሁለቱ ክልሎችና የፌዴራል ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የጸጥታ አመራሮች ተገኝተዋል።

ውይይቱ የተካሄደው ከአይጋሊ፣ ሞዛንቢስ፣ ኤዻር እና ዶቢ ቀበሌዎች ከተፈናቀሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር መሆኑም ታውቋል።

በውይይቱም በቀጠናው ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን  በአጥፊዎች ላይ አስፈላጊውን ሁሉ እርምጃ በመውሰድ እንደሚሰራም ተጠቁሟል።

ጉዳቱ የደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በበኩላቸው መንግስት በአካባቢው በዘላቂነት መፍትሄ በመስጠት ደህንነታቸውን እንዲያስጠብቅና  ሰብዓዊ ድጋፎች እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።

በተያያዘ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ዛሬ ጥቃት የደረሰባቸውን ቤተሰቦች ቡለን ወረዳ ዶቢ ቀበሌ በመገኘት አጽናንተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.