Fana: At a Speed of Life!

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትና ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በሀገር አቀፍ ምርጫ ዙሪያ ውይይት አደረጉ

አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በዘንድሮው ሀገር አቀፍ ምርጫ ቅድመ ዝግጅት ዙሪያ ውይይት አደረጉ።
 
ውይይቱ ተቋማዊ ነጻነታቸውና ገለልተኝነታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በሀገር አቀፍ ምርጫ ቅድመ ዝግጅት ለማድረግና በዓዋጁ ድንጋጌዎች ላይ የጠራ ግንዛቤ ለመያዝ ያለመ መሆኑን ከፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
 
ውይይቱ በምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ ቁጥር 1162/2011 ይዘትና አፈጻጸም፣ ወደ ፍርድ ቤት ሊቀርቡ በሚችሉ ጉዳዮች ዓይነትና ባህሪያት፣ የምርጫና ተያያዥ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ችሎቶች ስለሚደራጁበት አግባብ እና የዳኞች ስልጠና ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።
 
ከዚህ ባለፈም ፍርድ ቤቶች ከምርጫ ጋር ተያይዞ ለሚቀርቡላቸው አቤቱታዎች የሚሰጧቸው ውሳኔዎች የህዝብ አመኔታ እንዲኖራቸው፥ በተለይም ከድምጽ ቆጠራና ውጤት ጋር ተያይዞ ወደ ፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚቀርቡ አቤቱታዎች በአጭር ጊዜ ውሳኔ ስለሚያገኙበት ሁኔታ እንዲሁም የምርጫውን ሂደት ፍትሃዊነት የሚያረጋግጡ እንዲሆኑ ሊወሰድ ስለሚገባ ጥንቃቄ ተወያይተዋል።
 
በተጨማሪም በምርጫ አፈጻጸምና ጉዳዮች ላይ ሰፊና የተሻለ ልምድ ካላቸው የአፍሪካ ሃገራት ዳኞችና የምርጫ አስፈጻሚዎች፥ ከፍርድ ቤት ሚና አንጻር መልካም ተሞክሮ የሚቀስሙበት ሁኔታ በምርጫ ቦርድ በኩል እንዲመቻች አቅጣጫ ተቀምጧል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.