Fana: At a Speed of Life!

የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ምርጫ በሚካሄድበት ዕለት በከፊል ክፍት ሆነው ይውላሉ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 11 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ በሚካሄድበት ዕለት ከምርጫ ጋር የተያያዙ እና አጣዳፊ የፍርድ ቤት ውሳኔ የሚጠይቁ ጉዳዮችን ለማስተናገድ በከፊል ክፍት እንደሚሆኑ ተገለጸ።

የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ማለትም የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እና የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በምርጫና በፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ ከምርጫ ጋር የተያያዙ አለመግባባቶችን ለመዳኘት በተሰጣቸው ኃላፊነት መሰረት ከምርጫ ጋር የተያያዙ ጉዳዮቸን የሚመለከቱ በየደረጃው 26 ችሎቶችን አደራጅተው በነጻነት እና በገለልተኝነት ዳኝነት እየሰጡ ቆይተዋል።

በተመሳሳይም ሀገራዊው ምርጫ በሚካሄድበት ቀን የፍርድ ቤት ውሳኔን የሚሹ ከምርጫ ጋር የተያያዙ የወንጀልና የፍትሐ ብሔር ጉዳዮችን ለማስተናገድ በከፊል ከፍት ሆነው እንደሚውሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የላከልን መረጃ ያመላክታል።

በዚሁ መሰረት በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በሁሉም ምድብ ችሎቶች የድሬዳዋ ምድብ ችሎትን ጨምሮ የምርጫ ችሎቶች እና አራዳ ምድብ ችሎት የጊዜ ቀጠሮ ችሎት አገልግሎት የሚሰጡ ይሆናል።

በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ በዋናው ፍርድ ቤት በልደታ ምድብ ችሎት እና በአራዳ ምድብ ችሎት ለምርጫ ጉዳዮች የተደራጁ ችሎቶች ከፍት ሲሆኑ በተመሳሳይ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሁለት የምርጫ ጉዳይ ችሎቶች ዝግጁ ሆነው ይጠብቃሉ።

በሌላ በኩል በፌደራል ከፍተኛ እና መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በምርጫ ቀን ቀጠሮ ያላቸው ባለጉዳዮች በማግስቱ ማክሰኞ የሚስተናገዱ ሲሆን ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለባለጉዳዮች የሚስተናገዱበት ተለዋጭ የቀጠሮ ቀናት በፍርድ ቤቱ ድረ ገጽ እና በአጭር የጽሁፍ መልዕክት የሚገለጽ ይሆናል።

ፍርድ ቤቶች የሚቀርቡላቸውን ከምርጫ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ጉዳዮች በነጻነትና በገለልተኝነት ለመዳኘት ያላቸውን ዝግጁነት በመግለጽ ህዝቡ ተረጋግቶ እንዲመርጥ፣ ችግር ሲደጋጥምም ወደ ፍርድ ቤት እንዲያቀርብና የፍርድ ቤት ውሳኔን እንዲያከብርም ፍርድ ቤቱ ጠይቋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.