Fana: At a Speed of Life!

የፌዴራል ፍ/ቤቶች ለተጨማሪ 23 የስራ ቀናት በከፊል ዝግ ሆነው እንዲቆዩ ተወሰነ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 23 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ከአርብ መጋቢት 25 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ለተጨማሪ 23 የስራ ቀናት በከፊል ዝግ ሆነው እንዲቆዩ ተወሰነ፡፡

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዜዳንት ወይዘሮ መአዛ በሰጡት መግለጫ በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት አመላካቾች አስጊ መሆናቸውን ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት በመግለጽ ላይ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም ፍርድ ቤቶቹ ለተጨማሪ 23 የስራ ቀናት ማለትም ከመጋቢት 25 እስከ ሚያዚያ 30 ቀን 2012 ዓ.ም በከፊል ዝግ ሆነው እንዲቆዩ መወሰኑን አስረድተዋል፡፡

ወረርሽኙ የሚተላለፈው በአብዛኛው በሰዎች መካከል በሚኖር ንክኪ እና የተጠጋጋ ግንኙነት እንደሆነ ጉዳዩ በሚመለከታቸው አካላት የሚገለጽ መሆኑን ፕሬዚዳንትዋ÷ ከፍርድ ቤት የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ የሥራ ባሕሪ አንጻር ወረርሽኙ በፍርድ ቤቱ ማህበረሰብ እና በፍርድ ቤት ተገልጋዮች ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመከላከል የፌደራል ፍርድ ቤቶች ከመጋቢት 10-24 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ ለ15 ቀናት በከፊል ዝግ ሆነው እንዲቆዩ በተወሰነው መሠረት ይኸው ተፈጻሚ ሲሆን መቆየቱንም አስታውሰዋል፡፡

በዚህ ጊዜ ዳኞች ለውሳኔ የደረሱ እና ውዝፍ መዛግብት ላይ ውሳኔዎችን እየሰጡ እንደሚቆዩ፣ አስቸኳይ ጉዳዮችን በተለይም ከሰዎች መብት መከበር ጋር የተገናኙ፣ የሀገር ሰላምን እና ደህንነትን የተመለከቱ እና ወረርሽኙን በሚመለከት ሕጎች መከበራቸው አስፈላጊ ስለሚሆን እነዚህ እና መሰል ጉዳዮች በተረኛ ችሎቶች እንደሚታዩም ተነግሯል፡፡

የቆይታ ጊዜያቸው አንድ ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑ ለምርመራ የተቀጠሩ መዝገቦች በየቀጠሮ ቀናቸው እልባልት ተሰጥቶባቸው መዛግብቱ ወደ መዝገብ ቤት እንዲመለሱ ይደረጋል ያሉት ፕሬዜዳንትዋ በእስር ላይ የሚገኙ ተከሳሾችን ጉዳይ ቅድሚያ የመስጠት አስፈላጊ መሆኑንም መናገራቸውን ከፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ፍርድ ቤቶች በከፊል ዝግ ሆነው በሚቆዩባቸው ጊዜያት ውስጥ በወንጀል ጉዳዮች ላይ በሚሰጥ ፍርድ ምክንያት ከእስር መፈታት ያለባቸው ካሉ በሚመለከተው ችሎት በሚሰጥ ትዕዛዝ የሚፈፀም እንደሚሆንም ተገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.