Fana: At a Speed of Life!

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የትግራይ ክልልን በሚመለከት ውሳኔ አሳለፈ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 26፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የፌዴሬሽን ምክር ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ጉባዔ የፌደራል መንግስት ከትግራይ ክልል ምክር ቤት እና ከፍተኛ የህግ አስፈጻሚ አካል ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ማድረግ እንደማይቻል ወስኗል፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የህገመንግስት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ፀሐፊ አቶ ወርቁ አዳሙ በጉዳዩ ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በዚህም ፌደራል መንግስት ከትግራይ ክልል መንግስት ጋር ግንኙነት እንዳያደርግ ውሳኔ መተላለፉን ነው የተናገሩት፡፡

እንዲሁም የፌደራል መንግስት የትግራይ ህዝብን የሰላም የልማትና መሰረታዊ አገልግሎት ማዕከል በማድረግ ከወረዳ፣ ከከተማ ከቀበሌ አስተዳደሮች ጨምሮ በክልሉ ከሚገኘው ህጋዊ ተቋምማት ብቻ የስራ ግንኙነት እንደሚያደርግም ወስኗል፡፡

አቶ ወርቁ በመግለጫቸው የውሳኔው አፈጻጸምና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባዔ እና በሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ክትትል እንደሚያደርግም ነው የገለጹት፡፡

ይህ ውሳኔ የተወሰነው ከዚህ ቀደም በነሃሴ 30 ቀን 2012 ዓ.ም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ በወሰነው ውሳኔ መሰረት መሆኑ ተገልጻል፡፡

ከዚህ ቀደም የተወሰነው ውሳኔ የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት፣ አስፈፃሚ አካላት እና የምርጫ ኮሚሽን ምርጫን በሚመለከት ያወጣው አዋጅ፣ ያሳለፏቸው ውሳኔዎችና የፈፀሟቸው ተግባራት ከሕገ መንግስቱ ጋር የሚቃረኑ በመሆናቸው በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 9(1) መሰረት እንዳልተደረጉ የሚቆጠሩ፣ የማይፀኑ እና ተፈፃሚነት የሌላቸው ናቸው የሚል እንደነበር ይታወሳል፡፡

አዳነች አበበ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.