Fana: At a Speed of Life!

በምርጫ ቁሳቁሶች ላይ የሚፈፀምን ማጭበርበር ለመቀነስና ለይቶ ለማወቅ የሚያስችሉ እርምጃዎች ይፋ ሆኑ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለስድስተኛው ሃገራዊ ምርጫ በተዘጋጁ የምርጫ ቁሳቁሶች ላይ የሚፈፀምን ማጭበርበር ለመቀነስና ለይቶ ማወቅ የሚያስችሉ እርምጃዎችን ይፋ አደረገ፡፡
ለስድስተኛው ሃገራዊ ምርጫ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተደረገውን የቁሳቁስ ዝግጅት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና ተወካዮች ጎብኝተዋል።
በዚህ ወቅት እርምጃዎቹ ከዓለም አቀፍ ጥሩ ተሞክሮ እና ቀደም ሲል በሃገሪቱ ከተካሄዱ ምርጫዎች ልምድ በመውሰድ የተቀረፁ መሆናቸውን የቦርዱ የህዝብ ግንኙነት አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ ለፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች አስረድተዋል፡፡
አዳዲስ የጥንቃቄ ማድረጊያና ማጭበርበርን የመቀነሻ እርምጃዎች ይፋ የተደረጉ ቢሆንም የተወሰኑት ግን ሙከራውን የሚያበረታቱ በመሆኑ ይፋ ሳይደረጉ ይቆያሉም ብለዋል አማካሪዋ፡፡
በጉብኝቱ ደህንነቱ የተጠበቀ የቁሳቁስ መጋዘን፣ የመራጮች መዝገብ፣ ቁጥር የተሰጣቸው ማሸጊያዎች፣ መከፈታቸው የሚያስታውቁ ቦርሳዎች፣ የመራጮች ምዝገባ ካርድና ቀለም እንዲሁም የድምፅ መስጫ ወረቀት ቁሳቁሶች ላይ ያለውን የዘመናዊነትና ምቹነት ባህሪ በተመለከተ ገለጻ ተደርጓል፡፡
ይህም ቀላልና ዘመናዊ የድምፅ አሰጣጥ ስርአት እንዲኖረው ለማስቻል እንደሚያግዝ ተገልጿል፡፡
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ለገነባው ማዕከል የቁልፍ ርክክብ አከናውኗል፡፡
በዚህ ማዕከልም እየተቋቋመ የሚገኘው የሴት ፖለቲከኞች ምክር ቤትም የራሱ ቢሮ ያገኛል ተብሏል፡፡
በሶዶ ለማ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.