Fana: At a Speed of Life!

የ2020 የቤት ውስጥ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በኮሮና ቨይረስ ምክንያት ተራዘመ

አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በቻይና አስተናጋጅነት በናንጂንግ ሊካሄድ የነበረውን የ2020 የቤት ውስጥ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሀገሪቱ በተከሰተው በኮሮና ቨይረስ ምክንያት መራዘሙ ተገለፀ።

የ2020 የቤት ውስጥ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በቻይናዋ ናንጂንግ ከተማ አስተናጋጅነት ከፊታችን ከመጋቢት 4 እስከ መጋቢት 6 ድረስ እንደሚካሄድ ነበር የወጣለት መርሃ ግብር የሚያመላክተው።

ሆኖም ግን በቻይና ውሃን ግዛት በተከሰተው እና አሁን ላይ በሁሉም የቻይና ግዛቶች ታይቷል በተባለው የኮሮና ቫይረስ አማካኝነት ውድድሩ የሚካሄድበት ጊዜ እንዲራዘም መወሰኑ ነው የተነገረው።

የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ አስተዳዳሪ አካል ከጤና አማካሪዎቹ እና ከዓለም ጤና ድርጅት በተሰጠው ምክረ ሀሳብ መሰረት ውድድሩን በ12 ወራት ለማራዘም መወሰኑን አስታውቋል።

እንደ አትሌቲክስ አስተዳዳሪው አካል ገለፃ ውድድሩ የሚካሄድበትን ከተማ ለመቀየር ሀሳብ የቀረበለት ቢሆንም፤ ሆኖም ግን ቫይረሱ ከቻይና ውጪም በመከሰቱ እና ብዙ ሰዎች በአንድ ቦታ መሰብሰብ ደግሞ ለቫይረሱ ስርጭት አስተዋፅኦ ስላለው ከተማ መቀየሩን እንደ አማራጭ እንደማይመለከተው ገልጿል።

ውድድሩን በርካታ አትሌቶች የሚፈልጉት በመሆኑ እንደማይሰረዝ ያስታወቀው የዓለም አትሌቲክስ አስተዳዳሪ አካል፥ ውድድሩን በአውሮፓውያኑ 2021 የሚካሄድበትን ቀን ከናንጂንግ አዘጋጅ ኮሚቴ ጋር በመሆን እንደሚሰራበትም አስታውቋል።

የቤት ውስጥ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በየሁለት ዓመቱ እንደሚካሄድ ይታወቃል፤ በዚህም የአውሮፓውያኑ የ2018 በበርኒግሃም የተካሄደ ሲሆን፥ የ2020 በቻይና ናንጂንግ፣ የ2022 ደግሞ በቤልግሬድ እንደሚካሄድ ነው መርሃ ግብሩ የሚያመለክተው።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.