Fana: At a Speed of Life!

ዩኒቨርሲቲው መመረቂያ ጽሁፍ በሶፍትዌር አማካኝነት ተመርምሮ ከፕላጃሪዝም ነፃ መሆኑ ሳይረጋገጥ ዲግሪ እንደማይሰጥ ገለፀ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 21 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፀረ-ፕላጃሪዝም (Anti-Plagiarism) ፖሊሲ ከየካቲት 22 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚያደርግ አስታወቀ።
 
ከዚህ በኋላ ማንኛውም መመረቂያ ጽሁፍ በኧርከንድ (URKUND) በሶፍትዌር አማካኝነት ተመርምሮ ከፕላጃሪዝም ነፃ መሆኑ ሳይረጋገጥ ዲግሪ እንደማይሰጥ ዩኒቨርሲቲው ገልጿል።
 
ዩኒቨርሲቲው ፕላጃሪዝም አንድ የምረቃ ፅሁፍ የሚያዘጋጅ ወይም የምርምር ስራ የሚሰራ ሰው ሌሎች ሰዎች የሰሩትን ስራ የራሱ እንደሆነ አድርጎ በመውሰድ የአካዳሚክ እና የምርምር ሕግጋትን በመጣስ የሚፈፅመው ሕገወጥ ተግባር መሆኑን አስታውቋል።
 
ፕላጃሪዝም ተማሪዎች የመመረቂያ ጽሁፍ በሚያዘጋጁበት ጊዜ በራሳቸው ጥረት እና ልፋት የራሳቸው የሆነ ስራ ሰርተው እንዳያቀርቡ በማድረግ ዩኒቨርሲቲው ጥራትን ለማረጋገጥ በሚያደርገው ጥረት ላይ ትልቅ ጉዳት ሲያደርስ መቆየቱ ተጠቁሟል።
 
ይህ ችግር በመማር ማስተማሩና በምርምር ስራ ላይ በየጊዜው እያስከተለ ያለው አሉታዊ ተፅእኖ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ዩኒቨርስቲው በመገንዘቡ የፀረ-ፕላጃሪዝም ፖሊሲ ማውጣት አስፈላጊ ሆኖ አግኝቶታል፡፡
 
በመሆኑም ይህ ፖሊሲ ተግባራዊ ሲሆን ችግሩ እንደሚቃለል ዩኒቨርስቲው ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
 
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.