Fana: At a Speed of Life!

ደቡብ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጎን እንደምትቆም የአገሪቱ የውጪ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ም/ሚኒስትር ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ደቡብ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጎን እንደምትቆም የደቡብ ሱዳን የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ምክትል ሚኒስትር ዴንግ ዳው ዴንግ ገለጹ፡፡

በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ነቢል ማህዲ ከደቡብ ሱዳን የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ምክትል ሚኒስትር ዴንግ ዳው ዴንግ ጋር ተወያይተዋል፡፡

አምባሳደር ነቢል በደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት ትግበራ እየወሰደ ያለውን አዎንታዊ እርምጃዎች በተለይም የተዋሃደ ሰራዊት ለመመስረት እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ አበረታች መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በተፈጠረው ችግር የኢትዮጵያ መንግስት ሰብዓዊ እርዳታ ያለምንም ችግር እንዲደርስ፣ ጦርነቱ በሰላም እንዲፈታ አዎንታዊ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ይሁን እንጂ አሸባሪው ህወሓት ወጣቶችን አፍራሽ ለሆነ ዳግም ጦርነት እየቀሰቀሰ በመሆኑ ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ ይህንን ድርጊት እንዲያወግዝ ጠይቀዋል፡፡

የህዳሴ ግድብን በተመለከተ ችግሩን በአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር አደራዳሪነት በሶስትዮሽ ውይይት እና የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ጉዳይን በተመለከተ ሀገራችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እንደምትፈልግ አብራርተዋል፡፡

ምክትል ሚኒስትር ዴንግ ዳው ዴንግ በበኩላቸው÷ አሁን በኢትዮጵያ የተረጋጋ ሁኔታ መፈጠሩ አበረታች እንደሆነ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያ እንድትረጋጋ እየወሰዱት ያለውን ሰላማዊ አማራጭ እንደሚያደንቁ ገልጸዋል፡፡

በምዕራባውያን አንዳንድ ሚዲያዎችና አካላት ኢትዮጵያ ላይ የሚፈጥሩት ጫና በደቡብ ሱዳን ላይም ተመሳሳይ ችግር እያስከተሉ በመሆኑ ጉዳዩን በትክክል እንደሚረዱትና ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ መስጠት ነው ማለታቸውን በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.