Fana: At a Speed of Life!

ዳያስፖራው ማኅበረሰብ ለሀገሩ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን በሀገራቸው ዲኘሎማሲ ሠላምና ልማት ላይ የሚኖራቸው ሚና እና በጎንደር ከተማ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት እየተካሄደ ነው፡፡
አውደ ጥናቱ በጎንደር ዩንቨርስቲና በከተማ አስተዳደሩ እንደተዘጋጀም ነው የተመለከተው፡፡
በአውደ-ጥናቱ ላይ በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሰደር ብርትኳን አያኖ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ እና ሌሎች ባለሥልጣናት ተገኝተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱኳን አያኖ በአውደ ጥናቱ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ፥ በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን ሀገራችን ኢትዮጵያ የዲኘሎማሲ ፈተና በገጠማት ወቅት ለሀገራቸው ድምፅ በመሆን የሚያኮራ ተግባር ፈፅመዋል ብለዋል።
የአንዳንድ ሀገራትን ያልተገባ ጫና ለመቋቋም የተደረገው እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የነፃነት ፈላጊዎች በተለይም የአፍሪካዊያንና ወዳጆቻችን አጀንዳ እንዲሆን ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
ዲያስፖራዎች በፖለታካውና ዲኘሎማሲው ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚውና ማኅበራዊው ዘርፍም ከፍተኛ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልፀዋል።
በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን ለሀገራችው ኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።
የጎንደር ዩንቨርስቲ ኘሬዚዳንት ዶክተር አስራት አፀደወይን በበኩላቸው ፥ ዩኒቨርሲቲው የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማጥናትና በማማከር ዳያስፖራዎችን እንደሚያግዙ ተናግረዋል።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዘውዱ ማለደ ፥ የጎንደር ጥምቀትን ያደመቁ ዳያስፖራዎች ጎንደርን በልማት ተጠቃሚ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ጎንደር በርካታ የልማት ፀጋ ያላትና የጎረቤት ሀገራት መዳረሻ ስለሆነች በጎንደር ኢንቨስት ማድረግ ሀገርን ማሳደግ መሆኑን ከንቲባው ገልፀዋል።
የከተማ አስተዳዳሩ የሦስት ዓመት ኢንቨስትመንት ስትራቴጂ ማዘጋጀቱም ተመላክቷል፡፡
በኤልያስ አንሙት
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.