Fana: At a Speed of Life!

ዳያስፖራው ኢትዮጵያን የሚጎበኙበት መርሃ ግብር ተዘጋጀ

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 29፣ 2013 በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ከመጪው ጳጉሜን 1 እስከ ጥቅምት 15 ቀን 2014 ዓም ሀገራቸውን የሚጎበኙበት መርሃ ግብር መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት አስታወቀ።

የጉብኝት መርሃ ግብሩ “እንቁጣጣሽ ኢትዮጵያ የፍቅር ጉዞ ዓባይን እንጎብኘው” በሚል መሪ ሃሳብ ነው የሚካሄደው።
በመርሃ ግብሩ ዳያስፖራው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን እንደሚጎበኝና የግድቡን ሠራተኞች እንደሚያበረታታ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ አለባቸው ደሳለኝ ገልጸዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሃሳብ አመንጪነት ግንባታቸው የተከናወነው የሸገር ማስዋብና እንዲሁም በገበታ ለአገር ፕሮጀክት የተካተተው ጎርጎራ ይጎበኛሉ ብለዋል።

ዳያስፖራው በኢትዮጵያ የዳያስፖራ ሙዚየም ምስረታ ላይ አሻራውን የሚያሳርፍበት መርሃ ግብርም ይከናወናል።

ለጉብኝት የሚመጡት ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር እንደሚሳተፉም ነው አቶ አለባቸው ያስረዱት።

ዳያስፖራው ኢትዮጵያን ለአምስት ዓመት ለሚመራው መንግስት አደራ የሚሰጥበትና ከኢትዮጵያ ጎን መቆሙን የሚያረጋግጥበት ዝግጅትም ይኖራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሊቀመንበር አቶ አለማየሁ አበበ በበኩላቸው ጉብኝቱ ዳያስፖራው በኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች መዋዕለ ነዋዩን ለማፍሰስ ያለውን ፍላጎት ወደ ተግባር ለመቀየር የሚያስችል መደላድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።

በጉብኝቱ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ በተለያየ የሙያ መስክ የሚሰሩ ዳያስፖራዎች ለአገራቸው በምን ዘርፍ አስተዋጽኦ ማድረግ ይፈልጋሉ? በሚል ፍላጎታቸውን የሚያሰፍሩበት ቅጽ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

ይህም ከጉብኝቱ በኋላ ዳያስፖራው በኢትዮጵያ ሊሰማራባቸው ያሰባቸውን መስኮች ለማወቅ የሚያስችል እንደሆነ ተናግረዋል።

ምክር ቤቱ ዳያስፖራውን የሚያሳትፉ የተለያዩ መርሃ ግብሮች በዘላቂነት ለማካሄድ ማሰቡንም ነው አቶ አለማየሁ ያመለከቱት።

ጉብኝቱ ዳያስፖራው በኢትዮጵያ መሬት ላይ ያለውን እውነታ በማየት አገራቸው ያለችበትን ሁኔታ ለመረዳት መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ አለማየሁ ስለሺ ናቸው።
ዳያስፖራው ኢትዮጵያ ያለችበትን ተጨባጭ ሁኔታ ማየቱ የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንትና የልማት ስራዎች ለመመልከት ዕድል ይፈጥርለታል ብለዋል።

ጉብኝቱ ዳያስፖራው ከኢትዮጵያ ጎን መሆኑን የሚያሳይበት ዕድል እንደሚፈጥር የገለጹት አቶ አለማየሁ በመርሃ ግብሩ ለመሳተፍ ያለው ጉጉትና ፍላጎት የሚያድስበት መሆኑን ጠቁመዋል።

ዳያስፖራው አገሩን ለማገልገል ቆርጦ መነሳቱንና ኢትዮጵያ ከገባችበት ፈተና እንድትወጣ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት አባላቱ አመልክተዋል።

መንግስት ዳያስፖራው በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋዩን እንዲያወጣ የአሰራር ሂደቶችን ማሻሻልና መልካም ግንኙነት መፍጠር አለበትም ብለዋል።

“እንቁጣጣሽ ኢትዮጵያ የፍቅር ጉዞ አባይን እንጎብኛት” በሚል መሪ ሃሳብ በሚካሄደው የዳያስፖራው ማኅበረሰብ ጉብኝት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ አንድ ሺህ ዜጎች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት በመስከረም 2013 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎችን የያዘ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ምክር ቤቱ የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ በመገንባት፣ በኢትዮጵያ ልማትና በትውልድ ቀረጻ ላይ ትኩረቱን አድርጎ የሚሰራም ነው።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.