Fana: At a Speed of Life!

“ዴክሳሜታሰን” መድሃኒት ላይ ኢትዮጵያ ተጨማሪ ጥናቶችና ምክሮችን እያሰባሰበች መሆኑ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) “ዴክሳሜታሰን” የተባለው መድሃኒት በኮሮና ቫይረስ በፅኑ የታመሙትን ሰዎች ህይወት ለመታደግ ይረዳል መባሉን ተከትሎ ኢትዮጵያ ተጨማሪ ጥናቶች እና ምክሮችን እያሰባሰበች መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ከቀናት በፊት የብሪታኒያ ተመራማሪዎች በአነስተኛ ዋጋ በስፋት የሚገኘው “ዴክሳሜታሰን” የተባለው መድሃኒት በኮሮና ቫይረስ በፅኑ የታመሙት ሰዎች ላይ የሚከሰት የሞት መጠንን እንደሚቀንስ መግለፃቸው ይታወሳል።

መድሃኒቱ በተለይም በመተንፈሻ መሳሪያዎች (ቬንትሌተር) እና ኦክሲጅን ድጋፍ የሚተነፍሱትን ታማሚዎች የመሞት እድልን የሚቀንስ መሆኑንም ነው ተመራማሪዎቹ ያስታወቁት።

የዓለም ጤና ድርጅትም ዴክሳሜታሰን መድሃኒት በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ፅኑ ህሙማን ለማከም ጥቅም ላይ መዋሉን በበጎ እንደሚመለከተው በትናንትናው እለት አስታውቋል።

ኢትዮጵያም “ዴክሳሜታሰን” በተባለው መድሃኒት ላይ ተጨማሪ ጥናቶች እና ምክሮችን እያሰባሰበች መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

የጤና ሚኒስትር ዴታ ሳህረላ አብዱላሂ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተልን ነዉ ብለዋል።

ሚኒስቴሩ ጤናን በሚመለከት የተለያዩ አማካሪ ቡድኖች ጋር ይሰራል የሚሉት ሚኒስትር ዴታዋ፤ ከኮቪድ 19 በሀገሪቱ መከሰት በኋላም ይህ ከሀገር ውስጥ እና ዲያስፖራን በማካተት የሚሰራው አማካሪ ቡድንም የተለያዩ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን አንስተዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ የ“ዴክሳሜታሰን” መድሃኒት ጉዳይም መሆኑን በመግለፅ፤ በጉዳዩ ላይ ሚኒስቴሩን የሚያማክሩ ቡድኖች ክትትል እያደረጉ ነው ብለዋል።

ቡድኑም በመድሃኒቱ ላይ እያደረገ ያለውን የጥናት ውጤት እስከ ዛሬ ምሽት ለሚኒስቴሩ የሚገለጽ መሆኑን በመጥቀስ፤ በቀጣይነት ለህብረተሰቡ ይፋ ይደረጋልም ነዉ ያሉት።

እስከዛው ግን ህብረተሰቡ አላስፈላጊ ወጪ ከማውጣት በመቆጠብ የጤና ሚኒስቴር መግለጫን እንዲጠባበቅም ጥሪ አስተላልፈዋል።

ሚኒስትር ዴታ ሳህረላ አብዱላሂ አክለውም፥ በእጃችን ያለው የቫይረሱ መድሃኒት አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሁሉ ማድረግን ያለመሰልቸት መቀጠል ነው፤ ይህ ሲሆን የራስ ጥንቃቄ ለሌሎች የሌሎች ደግሞ ለሀገር ይተርፋል ብለዋል።

በአፈወርቅ አለሙ

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.