Fana: At a Speed of Life!

ዶናልድ ትራምፕ በሶማሊያ የሚገኙ የአሜሪካ ወታደሮች ሃገሪቱን ለቀው እንዲወጡ አዘዙ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 26 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሶማሊያ የሚገኙ የአሜሪካ ወታደሮች ሃገሪቱን ለቀው እንዲወጡ አዘዙ፡፡

ትራምፕ ወታደሮቹ እስከ ፈረንጆቹ ጥር ወር አጋማሽ ድረስ ሶማሊያን እንዲለቁ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን የሃገሪቱ መከላከያ መስሪያ ቤት አስታውቋል፡፡

የሶማሊያ ወታደሮች አልሸባብን እና ፅንፈኛ ታጣቂዎችን ለመዋጋት የሚያደርጉትን ጥረት የሚያግዙ ወደ 700 የሚጠጉ የአሜሪካ ወታደሮች በአካባቢው ይገኛሉ፡፡

ከእነዚህ ውስጥ አብዛኛዎቹ ሶማሊያን ለቀው የሚወጡ ሲሆን የተወሰኑት ደግሞ አሜሪካ ለምታካሂደው ድንበር ተሻጋሪ ዘመቻ በሶማሊያ ጎረቤት ሃገራት ይሰፍራሉ ነው የተባለው፡፡

ይሁን እንጅ ወታደሮቹ በየትኞቹ ሃገራትና መቸ እንደሚሰፍሩ የታወቀ ነገር የለም፡፡

የአሁኑ የትራምፕ ትዕዛዝ ግን በምስራቅ አፍሪካዊቷ ሃገር አሸባሪዎች ዳግም ያንሰራሩ ዘንድ እድል ይከፍታል በሚል በርካቶች ስጋታቸውን እየገለጹ ነው፡፡

ትራምፕ ከዚህ ቀደም በኢራቅ እና አፍጋኒስታን የሚገኙ የዋሽንግተን ወታደሮችን ቁጥር ለመቀነስ ተመሳሳይ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸው የሚታወስ ነው፡፡

በርካታ አሜሪካውያን በተለያዩ ሃገራት ለሰላም ማስከበር በሚል የሰፈሩ የአሜሪካ ወታደሮች ወደ ሃገራቸው እንዲመጡ በተደጋጋሚ ሲጠይቁ ነበር፡፡

ለዚህ ደግሞ በሃገራቱ አሜሪካ ያላት ጣልቃ ገብነት ኪሳራው የበዛ እና ውጤታማ ያልሆነ ነው የሚል ምክንያት ያቀርባሉ፡፡

ምንጭ፦ ቢቢሲ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.