Fana: At a Speed of Life!

ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ስልጣናቸውን በመጠቀም የሕወሓትን ዓላማ ማስፈጸማቸውን እንዲያቆሙ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ስልጣናቸውን በመጠቀም የህወሓትን ዓላማ ለማስፈጸም የሚያከናውኑትን ተግባር እንዲያቆሙ ዘጠኝ ተቋማት ለዳይሬክተሩ በጋራ በጻፉት ግልጽ ደብዳቤ ጠየቁ።
ደብዳቤውን የጻፉት የኢትዮጵያ ሕክምና ማህበር፣ የኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ማህበር፣ አሜሪካን ኢትዮጵያን ፐብሊክ አፌርስ ኮሚቴ (ኤፓክ)፣ ኢትዮጵያን ዳያስፖራ ሃይ ሌቭል አድቫይዘሪ ካውንስል ኦን ኮቪድ-19፣ ኢትዮጵያን ስኮላርስ ኢን ኖርዲክ ካንትሪስ፣ የደቡብ አፍሪካ የሕክምና ማህበር፣ የሌሴቶ ሕክምና ማህበር እና ፒፕል ቱ ፒፕል የተሰኙ ተቋማት ናቸው።
በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ግጭት የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተሩ ፖለቲካዊና ግልጽ ወገንተኝነት ያለው አካሄድን መከተላቸውን የጠቆሙት ተቋማቱ÷ በንግግርና በድርጊታቸውም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ላይ የተሳሳተና የተዛባ አቋም እንዲይዙ ማድረጋቸውን አመልክተዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ በሚሰጧቸው መግለጫዎች፣ በሚጽፏቸው ጽሑፎችና በማህበራዊ ትስስር ገጾቻቸው በሚያስተላልፏቸው መልዕክቶች÷ ህወሓት በአማራና አፋር ክልሎች በፈጸመው ድርጊትና በሕዝብ ላይ ባደረሰው መከራ ላይ ዝምታን መርጠዋል ብለዋል።
ህወሓት በፈጸመው ወረራ በርካታ የጤና ተቋማትን ማውደሙንና መዝረፉን አስታውሰው÷ ቡድኑ ንጹሃንን በመግደልና አስገድዶ በመድፈር ወንጀሎችን መፈጸሙን አመልክተዋል።
ዓለም አቀፍ ተቋማት ሳይቀሩ ህወሓት በክልሎቹ የፈጸመውን ድርጊት በሚያወጡት ሪፖርት እየገለጹ በሚገኙበት ወቅት ዶክተር ቴድሮስ በጉዳዩ ላይ ያሉት ነገር አለመኖር አድሎአዊነታቸው ለአንድ አካል የሚያሳይ እንደሆነ ነው ተቋማቱ በደብዳቤው ላይ የገለጹት።
ከጤና ሚኒስቴር ጋር በትብብር እንዲሰሩ በተደጋጋሚ ጊዜ ለሚቀርብላቸው ጥሪ ምላሽ አለመስጠታቸው የሚያሳዝን ተግባር ነው ብለዋል።
ህወሓት ወደ ትግራይ ክልል የሰብአዊ እርዳታ ለማድረስ እየተደረገ ያለውን ጥረት እያደናቀፈ እንደሚገኝ የጠቀሰው ግልጽ ደብዳቤው÷ ዶክተር ቴድሮስ በአሜሪካ በነበራቸው ጉብኝት ከባለስልጣናትና ከሕግ አውጪ ምክር ቤት አባላት ጋር ያደረጉት ውይይት ዓላማው በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ለመጎትጎት እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ጉብኝቱ የ’ኤችአር 6600’ እና ‘ኤስ 3199’ ሕጎች እንዲጸድቁ ግፊት ለማድረግ መሆኑን እንረዳለን ነው ያሉት ተቋማቱ።
ዶክተር ቴድሮስ የዓለምን ሕዝብ ጤና ለመጠበቅ የተሰጣቸውን ኃላፊነት የህወሓትን አላማ ለማስፈጸም እየተጠቀሙበት ነው፤ ከዚህም ድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል ብለዋል።
አፍራሽ የፖለቲካ እንቅስቃሴና የዘር ውግንናቸውን በመተው በሁሉም ኢትዮጵያውያን ጤና መጠበቅ ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሰሩ ተቋማቱ ጠይቀዋል።
ዘጠኙ ተቋማት በአማራና አፋር ክልሎች በህወሓት የወደሙ የጤና ተቋማትን መልሶ በማቋቋምና ሕክምና ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ድጋፍ ማድረጋቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.