Fana: At a Speed of Life!

ጀርመን አሽከርካሪ አልባ ባቡር ለህዝብ አገልግሎት አበቃች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ)የጀርመኑ ባቡር አገልግሎት ሰጪ ኩባንያ ዶቼ ባሀን ከሲመንስ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ጋር በመተባበር በዓለማችን የመጀመሪያ የሆነውን ያለ አሽከርካሪ የሚንቀሳቀስ ባቡር ይፋ አደረገ፡፡

በጀርመኗ ሀምቡርግ ከተማ ይፋ የተደረገው አሽከርካሪ አልባ ባቡር÷ ከሌሎች ባቡሮች አንፃር በሰዓቱ የሚገኝና ኃይልን ቆጣቢ ስለመሆኑም ተነግሮለታል፡፡

ከዚህ ቀደም እንደ ፓሪስ ያሉ ጥቂት ከተሞች ያለ ሰው በራሳቸው የሚንቀሳቀሱ ፈጣን ባቡሮች ጥቅም ላይ በማዋል ለዓለም አስተዋውቀዋል፡፡

የተለያዩ ኤርፖርቶችም እንዲሁ አሽከርካሪ አልባ ባቡሮች አሏቸው፡፡

የሀምቡርጉን ባቡር ግን የዓለማችን የመጀመሪያው አሽከርካሪ አልባ ባቡር ያሰኘው የተለየ መሠረተ ልማትን ሳይፈልግ ቀድሞ በተዘረጉት ሀዲዶች ላይ መንቀሳቀስ መቻሉ ነው፡፡

እስከ ዛሬ ድረስ የፓሪሱ እና ኤርፖርቶች አካባቢ ሲንቀሳቀሱ የተስተዋሉ ባቡሮቹ (Monorail) ግን ለየት ብሎ በተዘጋጀላቸው አንድ ነጠላ ሀዲድ ላይ ብቻ ነው መንቀሳቀስ የሚችሉት፡፡

የዚህ የተለየ ሀዲድ የማይፈልግ አሽከርካሪ አልባ ባቡር መምጣት የሀምቡርግን ፈጣን የከተማ ባቡር ስርዓት የማዘመን ፕሮጀክት አንዱ አካል ነው ተብሏል፡፡

በተጨማሪም ሌሎች አራት አሽከርካሪ አልባ ባቡሮች የከተማዋ ሰሜናዊ ፈጣን የባቡር መስመር እንደሚቀላቀሉ ታውቋል፡፡

አሁን በስራ ላይ ያለውን የባቡር መሰረተ ልማት ተጠቅመውም በቀጣዩ ወር ስራ እንደሚጀምሩ ተገልጿል፡፡

የሲመንስ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሮላንድ ቦች÷ አዲሶቹ ባቡሮች በ30 በመቶ የበለጡ ተሳፋሪዎችን የሚያስተናግዱ፣ ሰዓታቸውን በተሻለ ጠብቀው የሚያጓጉዙና የኃይል ፍጆታቸውም በ30 በመቶ ያነሰ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ባቡሮቹ በዲጂታል ቴክኖሎጂ አማካኝነት ቁጥጥር የሚደረግባቸው እና ያለ አሽከርካሪ የሚንቀሳቀሱ ቢሆንም፣ ተሳፋሪዎች ባሉበት ጊዜ ሁሉ ግን ጉዞውን የሚቆጣጠሩ አሽከርካሪዎች በውስጣቸው እንደሚኖር ነው የታወቀው ሲል ቴክስፕሎርን በመረጃ ምንጭነት ጠቅሶ ያመላከተው የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ነው፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.