Fana: At a Speed of Life!

ግብርናችንን ማዘመን የምግብ ዋስትናችንን ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን ሀገራዊ ብልጽግናችንን ማረጋገጥ ነው – አቶ ዑስማን ሱሩር

አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ)  በደቡብ ክልል የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ስራን በማዘመን የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተመለከተ።

ክልል አቀፍ የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት የንቅናቄ መድረክ በአርባምንጭ ከተማ እየተካሄደ ነው ።

በደቡብ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ እና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ዑስማን ሱሩር የንቅናቄ መድረኩን በንግግር ሲከፍቱ፥   ግብርናችንን ማዘመን የምግብ ዋስትናችንን ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን ሀገራዊ ብልጽግናችንን ማረጋገጥ ነው ብለዋል።

የደቡብ ክልል ለእንስሳት እና ዓሣ ሀብት ልማት ካለው ምቹነት አንጻር በሚሊየን የሚቆጠሩ አርሶ እና አርብቶ አደሮች በዘርፉ ለውጥ ማምጣታቸውን ነው አቶ ዑስማን የጠቆሙት።

እንደ አቶ ዑስማን ገለጻ፥ የግብርናው ዘርፍ ከነበረበት ኋላ ቀር የአሰራርና የአመራረት ስርዓት ወጥቶ  እንዲዘምን መንግስት ዘርፈ ብዙ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑንም አብራርተዋል።

የንቅናቄ መድረኩ ዋና ዓላማም የተሻሻሉ አሰራሮችን በመጠቀምና ግብርናን ወደ ቢዝነስ በመቀየር የክልሉን ህዝብ ሁለንተናዊ ህይወት መቀየር ነው ያሉት አቶ ዑስማን፥  አመራሩ በዘርፉ የሚያጋጥሙ ማነቆዎችን በመፍታት ለተሻለ ለውጥ እንዲተጋ ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በክልሉ የመኖ አቅርቦትን ተደራሽ በማድረግ የዳልጋ ከብቶችን ዝርያ ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው፥  ህብረተሰቡ እያረባቸው ያሉትን እንስሳት በተለያዩ አማራጮች በመጠቀም ዝርያውን በመደበኛ ሰው ሰራሽ ፣ በማዳቀል ቴክኖሎጂ እና በተፈጥሮ ኮርማ ማዳቀል ስራ ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል።

በዶሮ ሀብት ልማት ስራ በእንቁላል እና ስጋ ምርታቸው ውጤታማ የሆኑ ዝርያዎችን በማስፋፋት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማሳደግ ይገባልም ሲሉ አብራርተዋል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ ከረዥም ዓመታት ጀምሮ በባህላዊ መንገድ ሲካሄድ የቆየውን የንብ ማነብ ስራ፥  አርሶ አደሩ ተጠቃሚ እንዲሆን ዘርፉን ለማዘመን እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ የላከልን መረጃ ያመለክታል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.