Fana: At a Speed of Life!

ግብፅና ሱዳን የህዳሴ ግድብን  ለማስተጓጎል የያዙት አቋም ዓለም አቀፍ ህግን የጣሰ ነው- ምሁራን 

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 29 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ግብፅና ሱዳን ታላቁ የኢትዮጵያ   ሕዳሴ ግድብ ግንባታን ለማስተጓጎል የያዙት አቋም የዓለም አቀፍ የድንበር ተሸጋሪ ወንዞች አጠቃቀም ስምምነትን የጣሰ መሆኑን በአርባ ምንጭ  ዩኒቨርሲቲ የህግና  ውሃ ሀብት ምርምር   ምሁራን አስታወቁ።

በግድቡ ወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ኢዜአ ካነጋገራቸው ምሁራን መካከል በዩኒቨርሲቲው የህግ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ጋድሰንድ ኮኖሮ÷የተባበሩት መንግስታት በድንበር ተሸጋሪ ወንዞች አጠቃቀም ስምምነት ዙሪያ ያወጣው ህግ የተፋሰስ ሀገራት ፍትሐዊ አጠቃቀም መርህን እንዲከተሉ ያስገድዳል ብለዋል።

በተለይ የአንዱ መጠቀም በሌላኛው የተፋሰስ ሀገር ላይ የጎላ ተፅዕኖ በማያሳርፍ መልኩ መሆን እንዳለበትም ህጉ እንደሚያመለክት ገልጸዋል።

ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ እንደማንኛውም ሉዓላዊት ሀገር በግዛቷ የሚገኙ የተፈጥሮ ፀጋዎችን አልምታ የመጠቀም መብት እንዳላት አስረድተዋል።

ከተፋሰስ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን የሚያሳጣ ስምምነትና ቃል ኪዳን አለመግባቷን ጠቅሰዋል።

ግብፅ ከኢትዮጵያ በሚፈስ ውሃ የመጠቀም መብት እንዳላት ሁሉ ኢትዮጵያም በገዛ የተፈጥሮ ሀብቷ የማትጠቀምበት ምንም ምክንያት የለም ብለዋል።

ግብፅ እስካሁን የሄደችበት ርቀት በህዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት ከመተባበር ይልቅ ለማደናቀፍ የውሸት ትርክት ከመንዛት አንስቶ ብድር እስከ ማስከልከል  ጥረት ከማድረጓ ባሻገር ፀረ ኢትዮጵያ የሆኑ ቡድኖችን በገንዘብ ለመደገፍ  መንቀሳቀሷ  አስነዋሪ ተግባር  እንደሆኑ ምሁሩ አብራርተዋል።

የአባይን ወንዝ እኔ በብቸኝነት  ልጠቀም በሚል መውተርተሯና የላይኞቹ ተፋሰስ ሀገራትም እኔ ሰፍሬ በምሰጣቸው ልክ መጠቀም አለባቸው የሚል የተዛባ አቋም መያዟ የዓለም አቀፍ ህግን የጣሰ  መሆኑን አሰታውቀዋል።

በአንፃሩ የኢትዮጵያ መንግስት ከውሃ ድርድር ጋር በተያያዘ እያሳየ ያለው ቀናነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ከዓለም አቀፍ የውሃ አጠቃቀም ህጎችና መርሆዎች አንፃር ተቀባይነት ያለውና ተገቢ መሆኑን አስረድተዋል።

እንደ ምሁሩ  ገለፃ የህዳሴ ግድብ ከጎረቤት ሀገራት  ጋር የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠር፣ ለቀጠናው ሰላምና ብልፅግና ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው።

የተጀመረው የሦስትዮሽ ድርድር  የወንዙ ባለቤት የሆነችውን ኢትዮጵያ የመልማት መብቷን የሚያስከብር እንዲሆንና የታችኞቹ ተፋሰስ አገራት ጥቅምም የሚያስጠብቅ መሆን እንዳለበትም ተናግረዋል።

በዩኒቨርሲቲው የህግ ምሁር  ዘሪሁን ቦዳ በበኩላቸው÷ ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ ”ግብፅና ሱዳን የያዙት አቋም በዲፕሎማሲውም ሆነ ከህግ ተገቢነት አንፃር ፍጹም ተቀባይነት የለውም” ብለዋል።

ሱዳን እስካሁን ግልጽ አቋም ባለመያዟ ምክንያት በግብጽ መንግስት ጫናና ተፅዕኖ ስር በመውደቅ የግብፅን አቋም የማራመድና የመደገፍ አዝማሚያ ማሳየቷ ትዝብት ውስጥ የሚከታት ነው ብለዋል።

በአንፃሩ ከ80 በመቶ በላይ የአባይ ወንዝ ድርሻ ያላት ኢትዮጵያ ለብቻዬ ልጠቀም ሳትል ይልቁንስ በታችኞች ተፋሰስ ሀገራት ላይ ጉዳት በማያስከትል መልኩ በጋራ ለመጠቀም መወሰኗ ተገቢነትና ተቀባይነት እንዳለው አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ በድርቅ ምክንያት ህዝቧን ከተመፅዋችና  ከጭለማ ለማውጣት ግድቡን ጥቅም ላይ ማዋል የህልውና እና መብት ብቻ ሳይሆን የመንግስት ግዴታም ነው ብለዋል።

የግድቡ ግንባታ ዋና ዓላማ ውሃው ሃይል  ካመነጨ በኋላ የራሱን ፍሰት ይዞ የሚሄድ በመሆኑ  የሚያደርሰው ጉዳት እንደሌለ የገለጹት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የውሃ ሀብት ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ዶክተር ሳሙኤል  ዳጋሎ ናቸው።

‘በ21ኛው ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ እናቶች የማገዶ እንጨት በመሸከም ወገባቸው መጉበጡ ያሳዝናል  ያሉት ዶክተር ሳሙኤል÷ አሁን ላይ የሀገሪቱ የሃይል አቅርቦት  በቂ ባለመሆኑ በርካታ  ህዝብ ጭለማ ውስጥ እንደሚኖር አስረድተዋል።

እስከ አራት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ የግድቡን የውሃ ሙሌት ማጠናቀቅ እየተቻለ መንግስት እስከ 7 ዓመታት ደረጃ በደረጃ  ስለመሙላት ማቀዱ ምን ያህል ፍትሃዊ አካሄድን እየተከተለ መሆኑ አንዱ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚገባ  ዳይሬክተሩ አመልክተዋል።

ባለፉት ጊዜያት ከአባይ ወንዝ ጋር ተያይዞ  ሱዳን ለዘመናት በጎርፍና ደለል ስትናጥ መቆየቷን ጠቅሰው በቅርቡም በተፈጠረው የጎርፍ አደጋ የበርካታ ዜጎቿን ህይወት መንጠቁን አውስተዋል።

ሆኖም የግድቡ መገንባት ሱዳንንና ግብፅን ከጎርፍ እና ግድባቸውንም  ከደለል አደጋ ለመታደግ ጉልህ ሚና እንዳለው አምነው ሊቀበሉ እንደሚገባ  ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ሰፊ  የውሃ ሀብት ስላላት አባይን ትተውልን ማለታቸው  ጊዜ ያለፈበት ተረት በመሆኑ  ግብፅና ሱዳን ከግለኝነት አስተሳሰብ ተላቀው ለአባይ ዘላቂ ልማት ድጋፋቸውንና ትብብራቸውን ማሳየት እንዳላባቸው አመልክተዋል።

የግብፅ ምሁራን  የውሸት ወሬ እንደሚነዙት ሁሉ የኢትዮጵያ ምሁራንም ሳይንሳዊ እውነታን ይዘው ድምፃቸውን በማሰማት የበኩላቸውን እንዲወጡና ህዝቡም የጀመረውን ድጋፍ ከዳር እንዲያደርስም ምሁሩ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.