Fana: At a Speed of Life!

ጎግል በኮሮና ቫይረስ ዙሪያ መረጃ የሚያቀርብ ማንቂያ ወደ ስራ አስገባ

አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጎግል ስለኮሮና ቫይረስ መረጃዎችን ለማቅረብ የኤስ ኦ ኤስ ማንቂያን ወደ ስራ ማስገባቱን አስታወቀ።

ኩባንያው በትናንትናው ዕለት ወደ ስራ ያስገባው ማንቂያ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ አስፈላጊ መረጃዎችን ለማድረስ ያግዛል ተብሏል።

ስለኮሮና ቫይረስ እና ተያያዥ ጉዳዮች ሰዎች መረጃዎችን በሚፈልጉበት ወቅት ጎግል “በነጭ ካርድ መደብ” ላይ የኤስ ኦ ኤስ ማንቂያውን በማሳየት ተፈላጊውን መረጃ ለተጠቃሚዎቹ በቀጥታ ያጋራልም ነው የተባለው።

ጎግል ለዓለም አቀፍ መረጃ ፈላጊዎች በማንቂያው ላይ የዓለም ጤና ድርጅት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዳይሬክተር ጄኔራሎችን አድራሻ ማካተቱንም አስታውቋል።

አስፈላጊ ከሆነም በሂደት ማንቂያውን ለአካባቢያዊ መረጃ ፈላጊዎች በሚሆን መልኩ እንደሚያካትትም ገልጿል።

በቀጣይም ስለ ኮሮና ቫይረስ ጠቃሚ መረጃ፣ ያለበትን ሁኔታ እና ጥያቄና መልሶችን ያካተቱ አንቀጾች ያሉበት “የእርዳታ እና መረጃ” ማፈላለጊያን ከዓለም ጤና ድርጅት አድራሻ ጋር በማያያዝ አቀርባለሁ ብሏል።

ኩባንያው በአስፈላጊ እና ወሳኝ ወቅት ላይ ተጨማሪ የመረጃ ማሻሻያ እንደሚያደርግ በመግለፅ የማንቂያ ስርዓቱ ለኮሮና ቫይረስ ግብዓት የሚሆኑ መረጃዎችን በቀላሉ እንዲገኙ ያስችላል ነው ያለው።

በሞባይሎች እና ድረ ገፆች ላይ የሚገኘው ኤስ ኦ ኤስ ማንቂያ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ ችግሮች በሚፈጠሩበት ወቅት እንዲሁም በአጠቃላይ የሰዎች ደህንነት አደጋ ላይ በሚሆንበት ወቅት ጥቅም ላይ የሚውል ነው።

ከዚህ ባለፈም ኩባንያው ለቻይና የቀይ መስቀል ማህበር የ250 ሺህ ዶላር ድጋፍ ያደረገ ሲሆን፥ በመረጃ ማፈላለጊያ ገጹ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ በተከፈተ ዘመቻ ከ800 ሺህ ዶላር በላይ መሰብሰብ ተችሏል።

ምንጭ፦ ጎግል

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.