Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዐቢይ እና ፕሬዚዳንት ኢሳያስ የታላቁ ህዳሴ ግድብን ጎበኙ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 3 ፣2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በኢትዮጵያ በጋራ እያደረጉት ባለው ሁለተኛ ቀን ጉብኝታቸው የታላቁ ህዳሴ ግድብን ጎብኝተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በጉብኝታቸው የግድቡ ግንባታ ሂደት በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ መመልከታቸውን ገልፀዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ በዘንድሮው ዓመት አሁን ከያዘው በሶስት እጥፍ የሚበልጥ ውሀ እንደሚይዝም ነው የገለጹት።
በህዳሴ ግድቡ ግንባታ ላይ ለተሳተፉ እና አሁን ያለበት ደረጃ እንዲደርስ አስተዋፅኦ ላደረጉ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አሁን ያለበት ደረጃ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ኩራት መሆኑንም ተናግረዋል።
እስካሁን የተሠራው ሥራ ትልቅ ስኬት ቢሆንም በስኬቶች ከመኩራራት በየጊዜው አዳዲስ ግቦችን በመቅረፅ ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና ለመውሰድ እንደሚሠራም ነው የተናገሩት።
በዚህ ዓመት ግድቡ ከፍ እንዲል ማድረግ እና አሁን ካለው ውኃ ሦስት እጥፍ እንዲይዝ ለማድረግ የሚሠራ በመሆኑ ይህ ዓመት የግድቡ ዋነኛ ሥራ የሚሠራበት ነው ብለዋል።
በሌላ በኩል በዚህ ዓመት ኃይል ማመንጨት የሚጀምሩ ተርባይኖች ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመው÷ ተርባይኖቹ ለስድስት ወራት ሙከራ ካደረጉ በኋላ ሙሉ ለሙሉ ኃይል ወደ ማመንጨት ይገባሉም ነው ያሉት።
የግድቡን የግንባታ ሂደት የጎበኙበት ምክንያት የሥራውን እንቅስቃሴ ለማየት እና ወደ ፊት በግድቡ አካባቢ ለመስራት ለታቀዱት ከተሞች የአመቺነት ሁኔታን ለማየት እንደሆነም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት።
ግድቡ ሲሞላ ብዙ ደሴቶችን መፍጠር ስለሚችል ከወዲሁ ያንን እያዩ መዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑንም አውስተዋል።
የግድቡ ሁኔታ ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግና የምታደርገውን ጉዞ ውጤታማ እንደሚሆን ለሁሉም ወገን የሚያመላክት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ በየጊዜው ያንን በማረጋገጥ ስኬትን እውን ማድረግ አይቀርም ብለዋል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት ባለፈው ሐምሌ ወር ከተከናወነ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስፍራው ሲያቀኑ የአሁኑ የመጀመሪያቸው ነው ።
ሁለቱ መሪዎች በቆይታቸው የታላቁ ህዳሴ ግድብን አሁናዊ ገፅታን ተዘዋውረው የጎበኙ ሲሆን ÷ ገለፃ እንደተደረገላቸውም ኢቢሲ ዘግቧል።
መሪዎቹ ዛሬ ጠዋት የኮይሻ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብን መጎብኘታቸው ይታወሳል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.