Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከአውሮፓ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ጋር በስልክ ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከአውሮፓ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ቻርለስ ሚሼል ጋር በስልክ ተወያዩ።

በውይይታቸውም በቅርቡ በአውሮፓ እና አፍሪካ ህብረቶች የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን ተገናኝተው በተነጋገሩበት ወቅት ያነሷቸው ጉዳዮች የደረሱበትን ደረጃ መክረውበታል።

መንግስት የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦትን የበለጠ ለማሳለጥ ግጭት ማቆሙን ተከትሎ ወደ ትግራይ ክልል የሚገባው የሰብዓዊ እርዳታ መሻሻሉን መመልከታቸውን ፕሬዚዳንቱ አንስተዋል።

ፕሬዚዳንት ሚሼል ይህ ጥረት ከፍ ማለት እንደሚገባው በመናገርም፥ ተጨማሪ የየብስ መንገድ ቢከፈትና ቴሌኮሙኒኬሽንን የመሠሉ መሠረታዊ አገልግሎቶች ወደ ስራ ቢመለሱ ሲሉ ጠቁመዋል።

በግጭቱ ወቅት ለተጎዱ ሰዎች የሚቀርብ መሠረታዊ አገልግሎቶችን ለማሻሻል የሚውል የ81 ነጥብ 1ሚሊየን ዩሮ ድጋፍንም ይፋ አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በበኩላቸው የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭትን በፖለቲካዊ አማራጭ ለመፍታት የመንግሥትን ቁርጠኝነት አስታውቀዋል።

በውይይቱ ላይ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን እና የኢትዮ- ሱዳን ድንበር ጉዳዮችን ያነሱ ሲሆን፥ ግጭቶችን ለመፍታት የውይይት አማራጭን መምረጥ እንደሚገባ መመልከቱን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.