Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከኢንቨስትመንት እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ብሔራዊ ኮሚቴ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከኢንቨስትመንት እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ብሔራዊ ኮሚቴ ጋር ተወያዩ።

የውይይቱ ዓላማም ባለፈው ዓመት የተካሄዱትን ብሔራዊ የሥራ ዕድል ፈጠራ ክንዋኔዎች መመዘን እና ለቀጣዩ ዓመት አቅጣጫ መስጠት መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት አስታውቋል፡፡

ባለፈው ዓመት የተዋቀረው እና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሰብሳቢነት ሥራውን የሚከውነው ኮሚቴ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩን፣ የክልል ብሔራዊ መንግሥታት ፕሬዚዳንቶችን፣ የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተማ ከንቲባዎችን እንዲሁም ሁለት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ተወካዮችን በአባልነት አካትቷል፡፡

በአንድ ዓመት ውስጥ 3 ሚሊየን የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር ታቅዶ የነበር ሲሆን፥ የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን እንዳስታወቀው በሀገር አቀፍ ደረጃ በግብርና፣ በኢንደስትሪ እና አገልግሎት ሰጪ ዘርፎች 3 ሚሊየን 387 ሺህ የአጭር ጊዜ እና ዘላቂ የሥራ ዕድሎች ተፈጥረዋል፡፡

330 ሺህ የሥራ ዕድሎች የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተጽዕኖ ያረፈባቸው ቢሆንም፣ የደረሰባቸው ጉዳት የተገመተውን ያህል አስከፊ አይደለም ነው ያለው፡፡

የግሉ ዘርፍ የተጠናከረ ተሳትፎ፣ የመንግሥታዊ ፕሮጀክቶች መጠነ ሰፊነት፣ ለኢንተርፕራይዝ ዕድገት ትኩረት መስጠት እንዲሁም ለዘርፎች የሚደረግ የገንዘብ ድጋፍ ለዚህ ስኬት በዋነኛነት አስተዋጽዖ አድርገዋል፡፡

የመጪው 2013 ዓ.ም. የሥራ ዕድል ፈጠራ ዕቅድ በተመሳሳይ መልኩ 3 ሚሊየን የሥራ ዕድሎችን መፍጠር እና እስካሁን የተገኘውን ስኬት አጠናክሮ መቀጠል ነው ብሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግና የምታደርገው ጉዞ በልዩ ልዩ ኃላፊ ክስተቶች የተነሣ መቋረጥ እንደ ሌለበት እንዲሁም፣ የተገኙ ስኬቶችን እየመዘገቡ በዕድገት ጎዳና መገስገስ አስፈላጊ መሆኑን በአጽንዖት ተናግረዋል፡፡

ለመጪው ጊዜ አቅጣጫ በሰጡበትም ወቅት፥ ክልሎች በሙሉ ዐቅማቸው የጸጥታውን ዘርፍ ከማጠናከር ባለፈ ማኅበረሰቡ ባለ ድርሻ አካል እንደ መሆኑ ሰላምን በማስጠበቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣ በማድረግ ጸጥታ እና ደኅንነትን እንዲያሰጠብቁ አሳስበዋል።

ወጣቶች ኃይላቸውን ለበጎ ፈቃደኝነት ለማዋል የሚያስችላቸውን ጠንካራ አስተሳሰብ እና አቋም ማዳበር ላይ እንዲሠሩ፣ በጎ ፈቃደኝነትን ከቅጥር ቅድመ ሁኔታዎች መካከል አንዱ እንዲያደርጉ፣ የአውቶማቲክ ስልቶች ትግበራን እንዲያበረታቱ፣ በግል እና በመንግሥት ዘርፎች መካከል ትብብር እና መናበብ አጠናክረው እንዲያስቀጥሉ እንዲሁም የፋይናንስ ዘርፉን ለወጣቶች፣ ለአርሶ አደሮች እና አነስተኛ ትርፍ በሚያስገኙ ሥራዎች ለተሠማሩ ድጋፍ ለመስጠት በሚያስችል መልክ እንዲያጠናክሩም ነው ያሳሰቡት፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.